አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ የሰላም ምዕራፍ የሚከፍት ታላቅ እድል ነው።
በሀገር ውስጥ ያለውን ልዩነት በምክክር ለመፍታት አልሞ የተነሳው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚተርፍ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
የዚህ ምክክር ስኬታማነት መላውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ ብሩህ ተስፋና ዕድገት የሚመራ ታላቅ ስትራቴጂያዊ ርምጃ መሆኑን ነው ዋና ጸሀፊው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ ከበርካታ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ሰፊ ድንበር የምትጋራ እንደመሆኗ፥ በውስጧ የሚከሰት ማንኛውም የፀጥታ መናጋት ለጎረቤቶቿና ለቀጣናዊ አለመረጋጋት በር ይከፍታል።
ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን ከኃይል አማራጭ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል መሰረት የሚጥል በመሆኑ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ይህ ውስጣዊ ሰላም ድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ ስጋቶችንና የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት የጋራ አቅም በመፍጠር በጎረቤት ሀገራት ላይ የሚፈጠር ጫናን ያቃልላል።
ቀጣናዊ ተቋማት ቀውሶችን ለመፍታት ከመስራት ባሻገር በረጅም ጊዜ የጋራ ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብት፣ በሰው ኃይልና በንግድ አቅም የታደሉ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ በግጭቶች ምክንያት አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ መጠቀም አልቻሉም።
በኢትዮጵያ የሚገነባ ዘላቂ ሰላም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የንግድ ፍሰትን ለማሳለጥ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና በቀጣናው ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕሴቶቿን በመጠቀም የጀመረችው ይህ አዲስ ምዕራፍ ለጎረቤት ሀገራትም ቢሆን የፖለቲካ ልዩነቶችን ከኃይል አማራጭ ይልቅ በመመካከር መፍታት እንደሚበጅ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በውይይት የተመሠረተ የመፍትሄ ባሕልን በማጎልበት “የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ” የሚለውን መርህ በተግባር በማሳየት ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት በጋራ የመስራት አቅምን ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬት ለሰላምና መረጋጋት የሚያመጣው በጎ ተጽዕኖ ቀጣናውን ከጦርነትና ከድህነት አዙሪት አውጥቶ ወደ ዕድገትና ውህደት የሚያሸጋግር ዋነኛ ሞተር በመሆኑ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው የቀጣናው ሕዝቦች የጋራ ጉዳይ ነው፡፡
የዚህ ሂደት ስኬት የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው የአፍሪካ ቀንድ የጋራ ጥቅም መሆኑን በመረዳት ቀጣናዊ ተቋማትና የጎረቤት ሀገራት ይህንን ታሪካዊ የሰላም ጉዞ መደገፍ ይገባቸዋል።
በዮናስ ጌትነት

