Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከተማ አስተዳደሩ የበጀት ዓመቱን የማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳስታወቁት፥ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ በበጀት ዓመቱ የተቀመጡ ግቦች አፈጻጸም ይገመገማል፡፡

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ማጠቃለያ ዓመት መሆኑን ገልጸው፥ የበጀት ዓመቱን አፈፃፀም ከባለፉት 5 ዓመታት አፈፃፀም ጋር አያይዘን እንገመግማለን ነው ያሉት፡፡

ስትራቴጂክ ግቦቹን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በታማኝነትና በቅንነት ያለ እረፍት በመስራት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች አውጥተን የልማትና የሰላም ማዕከል አድርገናታል ያሉት ከንቲባዋ፥ በሰው ተኮር የልማት ስራዎች ከተማዋ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ፅዱ፣ አረንጓዴና ውብ እየሆነች መምጣቷን ጠቁመዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ስኬት ጀርባ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ በመድረኩ በተለይ የአመራሩ የውጤታማነት ልዩነት፣ በከተማዋ የሚታየው የኑሮ ውድነትና የፍልሰት ችግሮች በጥልቀት እንደሚገመገሙ አመላክተዋል፡፡

በርካታ ስኬቶችን ብናስመዘግብም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎትና ከብልፅግና ግባችን አንፃር ብዙ ስለሚቀረን ስኬቶቻችንን ማስፋት፤ ተግዳሮቶችን ለይተን በመፍታት በቀጣይ የላቀ ስኬት ማስመዝገብ የግምገማችን ማዕከል ይሆናል ብለዋል።

በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡

Exit mobile version