አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባሻገር ዓለምን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡
የዓለም ሀገራት ወሳኝ የሆኑ የዲጂታል ንግድ ልውውጦችን የባሕር በሮችን ተጠቅመው ያካሂዳሉ፡፡ ዲጂታል ግብይቶችና የመረጃ ልውውጦች የሚተላለፉባቸው የኢንተርኔት መስመሮች ሳይቀር መገኛቸው ባሕር ውስጥ ነው፡፡
የኢንተርኔት መስመሮች በባሕር እና በውቅያኖሶች ስር የተዘረጉ እንደመሆናቸው ኢንተርኔት ለመጠቀም ገመዶቹ ከየብስ አካላት ጋር የሚገናኙበትና ወደ ተጠቃሚው ህብረተሰብ መድረስ የሚችሉበት የባሕር በር ይፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ይህን በራሷ ማድረግ አይቻላትም፡፡
ዲጂታል 2025ን በስኬት አጠናቅቃ ዲጂታል 2030ን እየተገበረች ያለችው ኢትዮጵያ፤ ለዜጎቿ ፈጣን እና ሰፊ ተደራሽነት ያለው የዲጂታል አገልግሎት ለማቅረብ እየተጋች ትገኛለች፡፡
ሀገራችን ከንግድና ትራንስፖርት በዘለለ ግብ አድርጋ ላስቀመጠችው ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት የዲጂታል 2030 ጉዞ መተላለፊያ መንገድ የምትሻ በመሆኑ ወደብ ባለቸው ሀገራት ላይ ጥገኛ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡
ኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ የወደብ ባለቤትነቷን እንድታጣ በመደረጓ፣ የምንጠቀመው ኢንተርኔት የወደብ ባለቤት በሆኑ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት በኩል ማለፉ የግድ ነው፡፡
በጎረቤት ሀገራት ላይ የሚኖረን የኢንተርኔት መተላለፊያ ጥገኝነት ከሀገራት ጋር በሚኖር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲሁም በነሱ መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት ከመሆኑ ባሻገር የደህንነት ተጋላጭነት እና ስጋትን ስለሚፈጥር የመረጃና ደህንነት አቅምን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡
የባሕር በር አልባነት በሌሎች ላይ ጥገኛ እንድንሆን ከማድረግ ባሻገር የመወሰን አቅምን የሚያሳጣ በመሆኑ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እንቅፋት ይሆናል፡፡ ሉዓላዊነታችንንም ለአደጋ ያጋልጣል።
በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት፣ ሀገራት የኢንተርኔት መስመሮችን ለማቋረጥ ማስፈራሪያና ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባሕር መተላለፊያ መስመር ባለቤት መሆናቸው ይህን አቅም እንደሰጣቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡
ኢንተርኔት የማጣት ተግዳሮት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ የሚጎትት በመሆኑ የባሕር በር ለሀገር ኢኮኖሚዊ ጥቅም ከማምጣት ባሻገር ዓለምን መቆጣጠሪያና ሉዓላዊነትን ማስከበሪያ መሳሪያ እንደሆነ ይታመናል፡፡
በቤተልሔም ግርማ

