Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ግፋ” በኤርትራ፤ አፈሳ በትግራይ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤርትራን ወጣቶች ለዘመናት ሲያሰቃይ የኖረው የ”ሳዋ” ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ እና የ”ግፋ” (አፈሳ) መራር እውነት፣ ድንበር ተሻግሮ በኢትዮጵያ ምድር ዳግም ሲተገበር ማየት የታሪክ አሳዛኝ ክስተት ነዉ።

ትናንት የኤርትራ እናቶች በየመንገዱ እና በየቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ልጆቻቸውን ሲነጠቁ ያነቡት ዕንባ፣ ዛሬ በትግራይ እናቶች ጉንጭ ላይ ሲፈስ ማየት ያሳምማል።

ህገ ወጡ ህወሓት እና ሻዕቢያ፣ ምንም እንኳ በፖለቲካ ቼዝ ጠረጴዛ ላይ ደም አፋሳሽ ጠላቶች ቢሆኑም፣ በሕዝብ ላይ በሚተገብሩት የጭቆና እና የግዳጅ ምልመላ ስልት ግን “የርዕዮተ ዓለም መንታዎች” መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን ከእንጀራ አባቱ ሻዕብያ የወረሰዉ አንድ ጥሪት ቢኖር እሱም ጦርነትና ጭካኔ ብቻ ነዉ።

“ሳዋ” በትግራይ

በኤርትራ ከዓመታት በፊት የተተገበረው “ብሔራዊ አገልግሎት”፣ ወጣቶችን ዕድሜ ልክ ከሚያስረው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳዛኝ የስደት ታሪኮችን አስመዝግቧል። “ግፋ” በሚባለው የአፈሳ ዘመቻ፣ ወጣቶች ከትምህርት ቤት፣ መንገድ ላይ ወይም በቤታቸው እያሉ ተይዘው ወደ ሳዋ ይጋዛሉ።

ሴቶች መውልድን እስኪፈሩ፤ እናቶች ልጆቻቻውን መደበቂያ አጥተዉ እስኪሸበሩ ድረስ ሻዕብያ አዳጊ ልጆችን ከየመንደሩ እያፈሰ ለእሳት ሲማግድ ኖሯል። ከስልጣኑ በቀር ለምንም ደንታ የሌላቸዉ የአስመራው ጌታ፤ የህጻናትን ስስ ገላ ለሽያጭ ማቅረብ የደስታቸዉ ምንጭ ነዉ።

ኤርትራውያን ወጣቶች የሻእቢያን የፖለቲካ ግርድና ለመፈጸም፣ በየመን እና በሱዳን የጥይት እራት ሆነዋል። ከተከፈተው የሞት ደጃፍ ለመሸሽ ሲሞክሩ፤ በሰሃራ በረሃ አሸዋ ውስጥ የተቀበሩት እና በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው።

ይህ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ፣ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በትግራይ ክልል የሻዕቢያ ሎሌ በሆነዉ በህገ ወጡ ህወሓት መሪነት እየተደገመ ይገኛል።

ሻዕቢያ ቤት ለቤት እየዞረ ወጣቶችን ከእናታቸው እቅፍ እየነጠለ ለጦርነት እንደማገዳቸው ሁሉ፤ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድንም ህጻናትና አዳጊዎችን በተመሳሳይ መልኩ በግዳጅ እያፈሰ ነው። የትግራይ እናት በእንባ በራሰ ጉንጭ፤ በእንብርክክ እየተንፏቀቀች፤ አፈር በላይዋ ላይ እየነሰነሰች፤ ልጆቼን ተዉልኝ ብላ በመማጸኗ፤ የህገ ወጡ ቡድን ምላሽ የጥይት ሩምታ መክፈት ሆኗል።

ወጣቶች የህገ ወጡን ቡድን አፈሳ ሽሽት፤ ባገኙት ቀዳዳ እና አጋጣሚ ሁሉ ትግራይ ክልልን ለቀዉ እየወጡ ነዉ። በወጣቶች መስዋእትነት እድሜያቸውን ለመቀጠል የሚታገሉትን የህወሓት አዛውንቶች “በቃ” ያሉ ወጣቶችም ትግል ጀምረዋል።

ለግማሽ ምእተ ዓመት ትግራይን በደም ያጠቡት አዛውንቶች፤ በመቃብር አፋፍ ላይ ሆነዉም፤ የትግራይን ወጣት ጥይት ማብረጃ የማደረግ ህልም ከሁሉም አቅጣጫ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። የትግራይ ወጣቶችን ለሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በማከራየት በሀብት ላይ ሀብት ለመጨመር የሚፈጨረጨረውን ሃይል፤ ያሰባው ባይሆንለት የግብር አባቱ ሻዕብያን ጭካኔ ለመጠቀም መርጧል።

የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች

የሻዕቢያ እና የህወሓት የረዥም ዘመናት ትስስር ከበረሃው የትጥቅ ትግል ጀምሮ የተቀረጸ ነው። ሁለቱም ኃይሎች ማኅበረሰቡን የሚመለከቱት እንደ “ወታደራዊ ግብዓት” (Militarized Asset) እንጂ፣ እንደ ነጻ ዜጋ አይደለም።

ለእነዚህ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን ማረጋገጫው ሕዝብን በፍርሃት፣ በጥርጣሬ እና በማያቋርጥ የጦርነት ትርክት ውስጥ ማቆየት ነው።

በኤርትራ “የውጭ ጠላት አለብን” በሚል ትረካ ሳዋ ትውልድን ሲበላ እንደኖረው ሁሉ፣ በትግራይም በተመሳሳይ ወጣቱ ሌላ የሕይወት አማራጭ እንዳያስብ የማድረግ ስልታዊ ዘመቻ ተከፍቷል። የትግራይ ህዝብ ይበቃል እያለ ያለዉ ይህንን በወጣቶች ነብስና አካል የመጫወት ጭካኔ ነው።

Exit mobile version