አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ በነገው ዕለት በአዳማ ጨፌ አዳራሽ መካሄድ ይጀመራል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን በሰጡት መግለጫ÷ በጉባኤው ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ይገመገማሉ ብለዋል።
ጨፌው የስራ ዘመኑ መጨረሻ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ለሚመሰረተው አዲስ መንግሥት መደላድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በጉባኤው የ2018 ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተሰሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ቀርበው ምክክር የሚደረግባቸው ሲሆን፤ በጉባኤው መጨረሻም የተለያዩ ሹመቶች ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአቤል ነዋይ

