አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን ተከትሎ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ርምጃ ለሰባተኛ ምሽት ቀጥሏል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ማዘዣ (ሴንትኮም) እንደገለጸው፤ የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።
በዚህም በኢራን ወታደራዊ ሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶችን፣ የጦር መሣሪያዎችን ማከማቻ እንዲሁም የባህር ላይ አቅምን ለማዳከም ያለመ ርምጃ ተወስዷል።
ጥቃቱን ለመፈጸም አሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ድሮኖችን እና የጦር መርከቦችን መጠቀሟን ሴንትኮም ገልጿል።
ኢራን በሰጠችው አጸፋ ኩዌትን ጨምሮ የአሜሪካ አጋር ባለቻቸው ሀገራት ላይ ጥቃት ሰንዝራለች።
ቀደም ባለው ቀን መሰረተ ልማቶቼ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ያለችው ኢራን፤ በኩዌት የኤሌክትሪክ እና የውሃ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሷን አስታውቃለች።
የኩዌት ኤሌክትሪክና ውሃ ሚኒስቴር እንደገለጸው፤ የኤሌክትሪክ እና የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ የጥቃት ዒላማ ሆኗል ብሏል።
በአብረሃም አበራ

