አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ114 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው 2ኛው ምዕራፍ የሰሜን ተራሮች አይበገሬ የኑሮ ማሻሻያና ዘላቂ ስነምህዳር ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
በ458 ሚሊየን ብር የሚተገበረው ፕሮጀክቱ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችና 29 ቀበሌዎችን እንደሚያካትት ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አግማስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በሦስት ዓመታት በተተገበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች የፓርኩ ደህንነት ስጋት መቀነሱን ገልጸው፥ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ ትርጉም ባለው መንገድ መሻሻሉን አንስተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ይፋ በተደረገው ሁለተኛ ምዕራፍ በ30 ወራት ውስጥ 114ሺህ 941 ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ተፋሰሶችን ወደ ቀደመ ይዞታቸው መመለሰ፣ የኑሮ ምንጮችን ማስፋትና ማጠናከር፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ማበረታታትና የብሔራዊ ፓርኩን አስተዳደርና ጥበቃ ማጠናከር የፕሮጀክቱ ተቀዳሚ ዓላማ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ፕሮጀክቱ በኬር ኢትዮጵያ፣ ኦስትሪያ ልማት ኤጀንሲና አመልድ-ኢትዮጵያ የጋራ ትብብር የሚተገበር ሲሆን፥ ለስኬታማነቱ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።
በምናለ አየነው

