አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች፤ ይህም በጠረጴዛ ዙሪያ የመምከር፣ የመደማመጥና የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታን በውይይት የመቅረፅ ታላቅ ብሔራዊ የምክክር ስነ ህንጻ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ ከቃላት ድርደራ ባለፈ በተግባር መሬት ላይ ወርዶ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያን መፈራረስና ግጭትን ብቻ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጥሩ ኃይሎች “ምክክሩ አልተጀመረም” የሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ቢታዩም፤ እውነታው ግን ከዚህ ፍጹም የተገላቢጦሽ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ በመላው ሀገሪቱ እስከ ታችኛው የሕዝብ ክፍል ድረስ በመውረድና አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ሰፊ ሥራ አከናውኗል።
በአሁኑ ወቅትም የጉባኤው ተመካካሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውየማድረግ ሥራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።
ተወካዮችን 500 አባላት ባሏቸው ስምንት ቡድኖች በመክፈል በምክክር ሂደቱና በመጨረሻ ላይ ተለይተው የቀረቡት ስምንት ዋና አጀንዳዎች ያካተቷቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በኮሚሽነሮች አስተባባሪነት ገለጻ እየተደረገ ነው፡፡
የምክክር መርሆች፣ የሕገ ደንቦች አተገባበርና በሂደቱ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ለተሳታፊዎች በግልጽ እየተብራሩ ሲሆን፥ ይህ ሂደት ምክክሩ ምን ያህል ስር ነቀል እና አካታች መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ይህንን ታሪካዊ የሰላምና የውይይት ሂደት ለማደናቀፍ የሚተጉ የጥፋት አራጋቢዎች አሁንም አልጠፉም።
የሀገርን ስብራት ብቻ የሚመኙ፣ በግርግርና በትርምስ ውስጥ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚሹ የጥፋት ኃይሎች የጥፋት ድቤያቸውን እየደለቁ ነው።
የኢትዮጵያን መቁሰል እንደ ድል አድርገው የሚቆጥሩት እነዚሁ አካላት ዓይናቸው ላይ የጥላቻ መጋረጃ ስለተጋረደ የምክክሩን የመጀመር ብርሃን ለማየት አልታደሉም፡፡
ኢትዮጵያ ከውስጥ ያሉ ጥራዝ ነጠቆች ብቻ ሳይሆን ከውጭም ታሪካዊ ጠላቶች የሚያንዣብቡባት ሀገር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን እውነታና የሀገሪቱን የሰላም ጉዞ በተመለከተ ያስተላለፉት መልዕክትም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ቁመና በትክክል የሚገልጽ ነው።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል የሚነቁ፤ ያደፈጡ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ” በማለት በውስጥ መከፋፈል ለውጭ ጠላቶች በር ከፋች መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡት፥ የምክክር ጉባኤው በኮሚሽኑ የአሠራር ሥነ ዘዴ መሠረት እየተከናወነ ይገኛል።
ይህ የዋና ኮሚሽነሩ ማረጋገጫ ለእነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች መርዶ፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የአዲስ ምዕራፍ ብርሃን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚረጋገጠው በመናቆር ሳይሆን በመደማመጥ ነው።
በመሆኑም ሕዝቡ የጥራዝ ነጠቆችን የሐሰት ወሬና የጥፋት ድቤ ከቁብ ሳይቆጥር እውነትን አንግቦ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና በምክክሩ ሂደት ላይ በንቃት መሳተፉን ሊቀጥል ይገባል።
በኃይለኢየሱስ መኮንን

