አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የራሷ የሆነ መውጫና መግቢያን አስፈላጊነት የሚያጠይቅ ታሪካዊ መሰረት ያለው ነው፡፡
ጥያቄው የህልውና ጉዳይ ነው ሲባል፥ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ቀጣናዊ ተጽእኖን እና በአጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥ አጀንዳ በመሆኑ ነው፡፡
ከሀገረ ምስረታዋ ጀምሮ በቀጣናው የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ እጅግ ጥንታዊ የታሪክና የስልጣኔ አሻራ አኑራለች፡፡
በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የአዱሊስ ወደብ የዓለም አቀፍ ንግድ ማዕከል የነበረ ሲሆን፥ በቀጣዮቹም ዘመናት የባህር በር ባለቤትነቷ በምጽዋና አሰብ ወደቦች መዝለቅ ችሎ ነበር።
ሆኖም በታሪክ አጋጣሚ በተወሰነ የፖለቲካ ውሳኔና የጠላቶች ሴራ ምክንያት ከታሪካዊና ህጋዊ በሯ ከተነጠለች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦችን በማጣቷ ሙሉ በሙሉ የተዘጋች ሀገር ለመሆን የተገደደች ሲሆን፥ በዚህም የወጪና ገቢ ንግዷን ጨምሮ ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅሟ በሌሎች ሀገራት በጎ ፍቃድ ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጭ ንግዷን የምታካሂደው በጂቡቲ ወደብ በኩል ሲሆን፥ ይህም ለወደብ ኪራይና ሎጂስቲክስ በየዓመቱ በቢሊየን ለሚቆጠር ዶላር ወጪ ዳርጓታል፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ በምርት ዋጋ ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር የንግድ ተወዳዳሪነቷን የሚቀንስ ነው፡፡
የባህር በር አለመኖር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ፍሰት ያስተጓጉላል፤ በአንጻሩ የባህር በር ባለቤትነት የሀገር ውስጥ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር በር ይከፍታል፡፡
የሀገሪቱ የባህር በር ጥያቄ ከትራንስፖርት ወጪ ባለፈ ከሀገር ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው፤ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የፖለቲካ ወይም የጸጥታ መናጋት በሚፈጠርበት ጊዜ መላው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀላሉ እንዲታፈን ሊያደርግ ይችላል።
ኢትዮጵያ ወደ ታሪካዊ የባህር በር ባለቤትነቷ መመለሷ ጠንካራ የባህር ኃይልና የወደብ መዋቅር በመገንባት በቀይ ባህር ብሎም በቀጣናው የሚስተዋሉትን የባህር ላይ ወንብድናና ሽብርተኝነትን ከጎረቤቶች ጋር በጋራ ለመከላከል ሰፊ አቅም ይፈጥርላታል።
130 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በህዝብ ቁጥር ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር ስትሆን፥ ይህንን ታሪካዊ፣ ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊና አብሮ የመበልጸግ እሳቤን ባስቀደመ መንገድ ለመፍታት ሰፊ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የምታነሳው የባህር በር ጥያቄ ታሪካዊ መሰረት ያለው፤ እውነትና ፍትህን ደግሞም በጋራ የመልማት መሻትን የያዘ በመሆኑ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን ሕጋዊ የባህር በር ባለቤትነት ተነጥቃ እንደማትቀር ግልጽ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው እንዳሉት፥ ማንም ፈለገም አልፈለገም፤ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፡፡
በመልካም ፈቃዱ

