አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
በፍጻሜ ጨዋታው በወጣት ተጫዋቾች የተደራጀው የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከአርጀንቲና አቻው ጋር ኒውዮርክ በሚገኘው ሜትላይፍ ስታዲየም ይፋለማሉ፡፡
በአሰልጣኝ ሉዊስ ዴ ላፎንቴ የምትመራው ስፔን እስካሁን ባደረገቻቸው ጨዋታዎች በአንዱም ሳትሸነፍ በተጋጣሚዎቿ ላይ 13 ግቦችን አስቆጥራለች፤ የተቆጠረባት ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡
ስፔን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 2010 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን ÷ በድጋሚ በመድረኩ ለመንገስ ዛሬ በፍጻሜው ከአርጀንቲና ጋር የምታደርገው ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
አርጀንቲና እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቿ ላይ 19 ግቦችን ያስቆጠረች ሲሆን ÷ 7 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውባታል፡፡
ኳታር ያዘጋጀችውን የ2022 የዓለም ዋንጫን ያነሳችው አርጀንቲና በተከታታይ ዋንጫውን ለማሸነፍ የምታደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
ስፔን በታሪኳ ለ2ኛ ጊዜ እንዲሁም አርጀንቲና ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማሸነፍ የሚያደርጉት ትንቅንቅ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
በፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ተሸንፈው ጉዟቸው የተገታው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ትናንት ምሽት 6 ሰዓት ላይ ባደረጉት ፍልሚያ እንግሊዝ 6 ለ 4 በሆነ ውጤት አሸንፋለች፡፡
በታሪክ በብዙ ግቦች በታጀበውና እጅግ ምርጡ በተባለው የደረጃ ጨዋታ በርካታ ታሪኮች ተመዝግበውበታል፡፡
ቡካዮ ሳካ ሐትሪክ በመስራት የጨዋታው ምርጥ ተብሎ የተሸለመ ሲሆን ÷ ፈረንሳዊው ከሊያን ምባፔ 2 ግቦችን አስቆጥሮና አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
በዚህም ምባፔ በውድድሩ 10 ግቦችን በማስቆጠር ሲመራ ÷ ዛሬ ምሽት ለፍጻሜ የሚጫወተው ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ በ8 ግቦች ሁለተኛ ላይ ይገኛል፡፡
ምባፔ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች በአጠቃላይ 22 ግቦችን በማስቆር የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ እየመራ ነው፡፡ ዛሬ ምሽት የሚጫወተው ሊዮኔል ሜሲ በ21 ግቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሀገራቸው ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር እስካሁን በአንዱም ጨዋታ ያልታደሙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዛሬ ምሽቱን የፍጻሜ ጨዋታ በስታዲየም ተገኝተው ይከታተላሉ።
የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታው ማን ያሸንፋል ፤ ስፔን ወይስ አርጀንቲና ?
እንዲሁም የትኛው ተጫዋች ደምቆ ይወጣል ፤ የ8 ጊዜ ባሎንዶሩ አሸናፊ ሊዮኔል ሜሲ ወይስ በባርሴሎና የሜሲ አልጋ ወራሹ ላሚን ያማል የሚለው በምሽቱ ፍልሚያ መልስ ያገኛል፡

