አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኒውዮርክ ሰማይ ስር የእግር ኳስ ታሪክ አዲስ ንጉስ መውለዱን ለዓለም አውጇል።
የሊዮኔል ሜሲን የመጨረሻ ዳንስ ለመመልከት በተሰበሰበው የዓለም ሕዝብ ፊት ሳይጠበቅ የመጣው የስፔን የአዳጊዎች ስብስብ የክብር ዘውዱን ነጥቋል።
ይህ ድል የስፔን ብቻ አይደለም፤ በሜሲ እጅ ገላውን ታጥቦ ያደገው የላሚን ያማል የንግስና ዘመን ይፋዊ ማብሰሪያ ጭምር እንጂ፡፡
ታሪካዊው ፍልሚያ ከመጀመሩ በፊት ዓለም ሁሉ ትኩረቱን በሜሲና በአዳጊው ያማል የ2007 ድንቅ የፎቶ ትዝታ ላይ አድርጎ ነበር።
ሜሲ በበጎ አድራጎት መርሐ ግብር ላይ ገላውን ያጠበው የያኔው ሕፃኑ ያማል፥ ዛሬ በ19 ዓመቱ ድንቅ ጥበብ እያሳየ ለአርጀንቲና ፈተና ሆኖ ቀረበ።
በኒውዮርክ ስታዲየም የታየው ትዕይንት ድንቅ ነበር፤ ሜሲ ዘውዱን ለተተኪው አስረክቦ የዓለም ዋንጫውን ሲያጠናቅቅ ያማል ደግሞ አዲሱ የዓለም እግር ኳስ መሪ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህ የስፔን ወጣት ስብስብ በውድድሩ ጉዞው ቀላል አልነበረም።
ገና ከጅምሩ በጥንካሬና በማይበገረው የኬፕ ቨርዴ ስብስብ ብርቱ ፈተና ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፤ ያንን አስቸጋሪ ውቅያኖስ በፅናት ተሻግሯል።
ሜሲ እና የአርጀንቲናው ወርቃማ ትውልድ የስፔንን የወጣቶች ስብስብ የዋንጫ ጥማት ግን ሊገቱት አልቻሉም።
ቫሞስ! አዲሱ ዘመን ጀምሯል።
“ለሜሲ ያማል” የሚለው ድምጽ አሁን በስታዲየሙ ውስጥ ያስተጋባል።
በአንድ በኩል ለታላቁ ንጉስ ሜሲ የመጨረሻ ጉዞ የተሰማ ቁጭት ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ በላሚን ያማል መነሳት የተፈጠረ አዲስ እምቅ ስሜት ነው።
የስፔን ከዋክብት “ቫሞስ” እያሉ ዋንጫውን ወደ ሰማይ ሲያነሱ፥ እግር ኳስ አዲስ ምዕራፍ መጀመሯን አረጋግጣለች።
ታሪኩ ተፈጽሟል፤ ንጉሱ ሜሲ በታላቅ ክብር ተሰናብቷል፤ አዲሱ ንጉስ ያማል ደግሞ በኒውዮርክ ሰማይ ስር ዘውዱን ደፍቷል፡፡
በኃይለኢየሱስ መኮንን

