Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአሞራዎች ከንቱ ዙረት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የሰላምና ደህንነት፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ምሰሶ እና መሪ ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም የነፃነት እና የአንድነት ፅንሰ-ሀሳብ ማዕከል፣ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ መዲና እንዲሁም የኩራት ምልክት ስትሆን የአፍሪካን የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም የመፍታት አቅም እንዳላቸው በተግባር ያሳየች ሲሆን፤ ቀጣናውን በኢነርጂ ልማት እያስተሳሰረች ትገኛለች፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በመጠቀም ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
በዋናነት በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በንግድ እና ሌሎች የዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት የቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ እድገትን ከቃል ባለፈ በተግባር የገለጠች ሀገር ናት፡፡
ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና እድገት በተቃራኒው የቆሙ ታሪካዊ ጠላቶች አሁንም ኢትዮጵያን ከቀጣናዊ ትብብሮች ለመነጠል እና አህጉራዊ መሪነቷ ለማስቆም ሙከራ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡
በትናንትናው እለትም የካይሮ እና የአስመራ ፈረሶች ከኢትዮጵያ በላይ ለቀጣናው አሳቢ በመምሰል በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር ደህንነት እና ቀጣናዊ ትብብር በጋራ መከርን ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
ግብፅ እና ኤርትራ ግንኙነታቸው ለቀጣናው የሚጠቅም ትብብር ወይም ለቀይ ባህር የጋራ ሰላም ፋይዳ ያለው ስምምነት ለመፈፀም ሳይሆን እኩይ ቀጣናዊ ፍላጎታቸውን ለማሳከት ያለመ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ቁራጭ ስጋ ፈልገው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚያንዣብቡ አሞሮች ኢትዮጵያ ካልፈቀደች ምንም አያገኙም።
ኢትዮጵያ አሁንም ለአሞራዎቹ ከንቱ ዙረት እና ለባንዳዎች ጩኸት ትኩረት ሳትሰጥ ዘላቂ ሰላሟን ለማረጋገጥ እና ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ስራ ላይ ነች።
በሚኪያስ አየለ
Exit mobile version