አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ካረጀውና በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ከተደገፈው የግብርና ምህዳር በማውጣት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስትራቴጂን ቀረጸ።
በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች፡ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ አይሲቲ እና አምራች ኢንዱስትሪ ተለይተው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች በገባው ቃል መሰረት በርካታ ስኬት አስመዝግቧል።
በተለይም በግብርና ዘርፍ ግብርናው ማዘመን፣ የምግብ ዋስትናን (ራስን መቻል) ማረጋገጥ እና ኢትዮጵያን ከእህል አስመጪነት ወደ ላኪነት ማሸጋገር ላይ ከፍተኛ ድል ተመዝግቧል።
ግብርናው በመደመር መንግሥት ስር ትልቅ የመዋቅር ለውጥ አሳይቷል፤ በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተመዘገበው ውጤት ሀገራዊ ብልጽግናን እውን የማድረግ ውጥንን ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
በግብርና ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል አሁንም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የመኸር ወቅት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሰብል ምርት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚሸፍን በመሆኑ ለሀገራዊ የልማት ጉዞ የማይተካ ሚና ይጫወታል።
በዚህ ምክንያት የመኸር እርሻ በየዓመቱ በመንግሥት፣ በአርሶ አደሮች፣ በግሉ ዘርፍና በልማት አጋሮች ትኩረት የሚያገኝ ዋና የልማት አጀንዳ ሆኗል።
የመኸር እርሻ የተሳካ ሲሆን የምግብ ዋስትናን ከማጠናከር ባለፈ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ለማረጋገጥና የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን እውነታ በመገንዘብ የመኸር እርሻን በሀገራዊ የልማት እቅዶቹ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አስቀምጦታል።
የግብርና ግብዓቶች በወቅቱና በበቂ መጠን ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ፣ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች እንዲስፋፉ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲጠናከር እና ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሰራ ነው።
የመኸር እርሻ ስኬት በከፍተኛ ደረጃ በግብዓት አቅርቦት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ መንግሥት በምርጥ ዘር፣ በማዳበሪያ፣ በፀረ-ተባይ መድኃኒቶች፣ በእርሻ ማሽነሪዎች እና በቴክኒክ ድጋፍ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
የግብዓት ግዥና ስርጭት ከክልል መንግስታት፣ ከህብረት ስራ ማህበራት፣ ከዩኒየኖች እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ይከናወናል።
ዓላማውም ግብዓቶች በትክክለኛው ጊዜ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱና የእርሻ ስራው ያለምንም መጓተት እንዲከናወን ማድረግ ነው።
አሁን ላይ ከግብዓት አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት የመንግስት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ሆኗል።
የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች፣ የእርሻ ማሽነሪዎች፣ ዘመናዊ የውሃ አስተዳደር ዘዴዎች፣ ዲጂታል የግብርና መረጃ ሥርዓቶችና የአፈር ምርመራን መሰረት ያደረጉ የማዳበሪያ አጠቃቀም ልምዶች በስፋት እንዲዳረሱ እየተሰራ ነው።
ይህም በአንድ ሄክታር የሚገኘውን ምርት ከፍ ከማድረግ ባለፈ የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪና ዘላቂ ለማድረግ ያስችላል።
በአመለወርቅ ደምሰው

