Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወሳኙ ታሪካዊ ዕድል ሀገራዊ ምክክር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታትና የሀገር አንድነትን ለማጠናከር ዋነኛ መፍትሄ ነው፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል የነበሩ አለመግባባቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባሕል የፈጠረ ነው፡፡

ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ አካላት እንኳን የያዙትን አጀንዳ ይዘው በሰላማዊ መንገድ እንዲወያዩ ዕድል የፈጠረና ታሪካዊ መሰናክል የታለፈበት ሒደት መሆኑን አሳይቷል።

ሀገራዊ ምክክሩ ከነበርንበት ችግርና መከራ መውጫ መንገድ ሆኖ ባለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ ምዕራፎችን በማለፍ ለሀገራዊ መግባባት መሰረት የሚጥል አጀንዳዎችን ለይቷል።

በዚህም ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በመለየት ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ አሰባስቦ ሀገራዊ ምክክር ከተጀመረ እነሆ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

ችግር የሚፈጠረውም ሆነ የሚፈታው በሰው በመሆኑ ሀገራዊ ምክክሩ ጥያቄን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል መንገድ ላይ ገብቷል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በ80 ንዑስ ቡድኖች ያደራጀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውይይት ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንዳሉት÷ የተጀመረው የንዑስ ቡድን ውይይት የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።

ምዕራፉ ተመካካሪዎች በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበትና አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ በሰለጠነ መንገድ የሚመካከሩበት ሂደት እንደሆነም ገልጸዋል።

እያንዳንዱ ዐቢይ የሥራ ቡድን 50 ተመካካሪዎች ያሉባቸው 10 ንዑስ ቡድኖችን የያዘ ሲሆን÷ በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ዝርዝር ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

ተመካካሪዎቹ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በኮሚሽኑ ይፋ በተደረጉት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተመድበው የቅድመ ምክክር ውይይቶችን፣ የጋራ ትውውቆችን እና በምክክሩ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ አስፈላጊውን ግንዛቤ ወስደዋል።

Exit mobile version