Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብሔራዊ ጥቅማችን ቀይ መስመር

የማንኛውም ሀገር መሠረትና የህልውና ዋስትና የሆነው ብሔራዊ ጥቅም ከማንኛውም ድርድርና ስምምነት በላይ የሚቆም ቀይ መስመር ነው፡፡

ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትን፣ የሕዝብን ደህንነትና ስልታዊ ሀብቶችን ማስጠበቅ ሀገራት በየትኛውም ሁኔታ አሳልፈው የማይሰጧቸው ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሀገራት ለብሔራዊ ጥቅማቸው መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች በመለየት በትኩረት ይሰራሉ። በዚህም የቆሙበትን ጽኑ መሰረት እያጠናከሩና እያስጠበቁ ይሄዳሉ።

የውሃ ደህንነት፣ የባህር በር አጀንዳ እና ብሔራዊ መግባባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያና ማጠናከሪያ መሰረቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ጉዳዮች ከሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፣ የህዝብ ደህንነትና ህልውና፣ ስልታዊ እና የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ብሔራዊ ክብርና ታሪክ ጋር ተሳስረው ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ወሳኝ ናቸው።

ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመውጣት እና የኢኮኖሚ ደህንነትን ለመጠበቅ ስልታዊ የባህር በሮችን ማግኘት ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው።

የቀይ ባህር መስመር ለዓለም ንግድ ወሳኝ በመሆኑ፣ በአካባቢው ካሉ ሀገራት እና በዓለም አቀፍ ኃይሎች ዘንድ የባህር መስመሩን ደህንነት ማስጠበቅ ለድርድር አይቀርብም። ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ብሔራዊ አጀንዳ ያደረገችበት ምክንያት ከዚሁ ጋር ይያዛል።

ግብፅና ኤርትራ ‘የቀይ ባህር ደኅንነትና አስተዳደር የሚመለከተው ከባህሩ ጋር የሚዋሰኑ ሀገራትን ብቻ ነው’ የሚል አቋም በመያዝ የቀጣናዊ ሰላም በዘላቂነት ቀውስ ውስጥ ሊከት የሚችል አቋም ማራመድ ጀምረዋል፡፡

የሀገራቱ አቋም የኢትዮጵያን የባህር በር ህጋዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ የባለቤትነትና የመጠቀም መብት ለመንፈግ ያለመ መሆኑ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያን ከቀጣናው ለማግለል እና ከበባ ውስጥ ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት ለመስበርና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መቆም ይጠበቅበታል።

ሀገራት እና ዜጎቻቸው ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ለድርድር እንደማያቀርቡ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለድርድር አያቀርቡም፡፡

በኢትዮጵያ እንደ ብሔራዊ ጥቅም የሚታዩ ጉዳዮች ላይ የእኛ የዜጎች አቋም መጠናከር አለበት። በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ምሁራኖቻችን፣ የፖለቲካ ተዋንያን፣ ተቋማት፣ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ያለልዩነት ይህ ቀይ መስመሬ ነው አትንኩብኝ የሚለው ጉዳይ ሊኖረው ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከሀገር ፍቅር ስሜት ጋር መታየት አለበት፡፡ በዚሁ መሠረት ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ቆጥረን ቀይ መስመር ማስመር ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም የፓርቲ፣ የስልጣን ወይም የጊዜያዊ ፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ህልውናና የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን የጋራ አጀንዳ ነው።

ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷና በስልታዊ የባህር በር ፍላጎቷ ላይ ያላት አቋም ድርድር የማይደረግበት ሀገራዊ ቀይ መስመር ሊሆን ይገባል።

ስለሆነም ዜጎች፣ ምሁራን እና የፖለቲካ ተዋንያን ልዩነቶቻቸውን በመተው ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም እና የሉዓላዊነት ከፍታ በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው ጽሑፉ አበክሮ ያሳስባል።

Exit mobile version