አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዕለት የዕለቱን ብቻ በሚያስብ፣ ነገን አሻግሮ ማየትና ማሳየት ባልታደለ መንግሥትና ወደ መጪው ትውልድ ማማተር ባልፈቀደ ሕዝብ ጠንካራ እና የበለጸገች ሀገር መገንባት ያዳግታል።
ዛሬ ላይ ልዕለ ሀያላን የሚባሉ ሀገራት በየዘርፉ የደረሱበት ከፍታና ጠንካራ የሀገር ግንባታ በዕለት አጀንዳ ከመጠመድ ይልቅ በርካታ አስርት ዓመታትን ቀድመው ተጉዘው መሆኑን ልብ ይሏል።
አሜሪካ ግዛቶቿን በፈጣን መንገዶች በማስተሳሰር ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረቷ የሆነው “ኢንተርስቴት ሀይዌይ ሲስተም” የተሰኘው ፕሮጀክት 7 አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የሀገሪቱ ንግድ ጽኑ ምሰሶ ሆኖ ዘልቋል።
ቻይና ከፈረንጆቹ ከ197ዐዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በኢንዱስትሪ፣ በፈጣን ባቡር መስመሮች፣ በወደቦችና በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ያደረገችው የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ዛሬ ከዓለም ትልልቅ ኢኮኖሚዎች አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል።
የመደመር ትውልድ በዛሬ የታጠረ አይደለም፤ ትናንት ባመለጡን ዕድሎች የሚቆዝምም አይደለም፤ ይልቁንም ከቀደሙት ስህተቶች በመማር ነገን ዛሬ ለመስራት የቆረጠ ትውልድ ነው።
በትውልዶች ቅብብሎሽ ሺህ ዓመታትን የተሻገረችው ሀገራችን ስለ ነገው ትውልድ ጭምር በሚገደው የመደመር መንግሥት መሪነት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይናጉ ተቋማትን በመገንባት ላይ ትገኛለች።
በአንድ ሀገር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ጠንካራ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማትን ለመገንባት ውጤታማ ሪፎርም ተተግብሯል፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ በከፍተኛ ዝግጅት ሲከናወን የቆየው የሀገራዊ ምክክር አሁን ላይ ወደ ዋናው የምክክር ምዕራፍ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ይህ ምክክር ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ሰላማዊት ሀገር እንዲሁም አለመግባባቶችን በመመካከር መፍታት የሚቻልበትን ቁልፍ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍበት ነው፡፡
የመደመር መንግሥት በአንድ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ ሳይወሰን ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ገቢራዊ በማድረግ የዛሬን ችግሮች ከመፍታት ባሻገር ለትውልድ የሚተርፉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቷል፤ እየገነባም ይገኛል።
ትውልድን አልመው በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች እየተተገበሩ ያሉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ለማዘመን፣ ከተሜነትን በአግባቡ ለማስተዳደር የተወጠኑ ናቸው፡፡
በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጊዜያዊ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ትውልድ ተኮር ፕሮጀክት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ የኮሪደር ልማት ውብ እና ለኑሮ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ከመፍጠር ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ ፍላጎት የተስማሙ ከተሞችንና መንደሮችን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡
ከጥገኝነት ሳይላቀቁ ለትውልድ የሚሻገር ኢኮኖሚን መገንባት እንደማይቻል ልብ ያለው የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የግብርና አቅም በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ የሚያስችሉ ንቅናቄዎችን በልዩ ትኩረት ተግባራዊ አድርጓል፡፡
እነዚህ ንቅናቄዎች ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የግብርና ስርዓትን በዘላቂነት ለማዘመን የሚያስችሉ ሲሆን፥ ለአብነትም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን የእርሻ ባህል በመቀየር በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት አስደናቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ የስንዴ ፕሮግራም ምርታማነትን በመጨመር፣ የመስኖ ሥርዓትን በማስፋት፣ የዘር አቅርቦት ሥርዓትን በማጠናከር ብሎም በዋና ዋና አካባቢዎች አነስተኛ አርሶ አደሮችን በመደገፍ ራስን የመቻል ጉዞ ግብ ላይ የተመሠረተ ነው።
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ የመስኖ ስንዴ ምርትን ሳይጨምር 126 ነጥብ 69 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡
በጥቅሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን 29 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፥ በዚህም የግብርና ዘርፉ የ7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን እንዲሁም የአቡሴራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ መጪዎቹን በርካታ አስርት ዓመታት ታሳቢ ያደረጉ የልማት ሥራዎች እየተከወኑ ይገኛሉ፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

