Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕገ-ወጡ ሕወሓት አዲሱ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ እና የትግራይ ሕዝብ እምቢተኝነት

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ፣ የክልሉንም ጊዜያዊ አስተዳደር አፍርሷል።

ይህ ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማጥቃት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው።

ሆኖም፣ የትግራይ ሕዝብ ለጦርነት እምቢተኛ መሆኑን በአደባባይ እያሳየ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት እና የሕወሓት አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙት ታሪካዊ የሰላም ስምምነት፣ የሁለት ዓመቱን ግጭት አስቁሞት ነበር።

ስምምነቱ ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ያለመ ቢሆንም፣ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ግን ስምምነቱን በመጣስ የክልሉን ሰላም አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል።

ቡድኑ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስና ራሱ ስልጣን በመቆናጠጥ ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሀገሪቱን ወደ አዲስ ጦርነት ለመክተት እየሰራ መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የራሱ የሕገ-ወጡ ቡድን መሪዎችም በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ይህንን አምነዋል፡፡

በሕገ-ወጡ ቡድን የሚካሄደው ይህ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ የትግራይን ሕዝብና ወጣቶች ለአፈናና ለከፍተኛ አደጋ እየዳረገ ነው።

ለዚህ እኩይ ተግባር እውቅና የማይሰጠው የትግራይ ሕዝብ፣ ዳግም ለትርጉም አልባ እልቂትና ውድመት የሚዳርገውን አካሄድ በከፍተኛ ደረጃ እየተቃወመ ይገኛል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ እና የህዝብ ተቃውሞ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

በሰልፉ ለትግራይ ህዝብ አሁን ላይ የሚያስፈልገው የጦርነት ነጋሪት ሳይሆን ሰላም፣ ልማት፣ ሥራ ዕድል እና የኢኮኖሚ መረጋጋት መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ሕወሓት በክልሉ እያደረገ ያለውን የግዳጅ ወታደራዊ ቅስቀሳ እና የጦርነት ዝግጅት በበራሪ ወረቀቶች አማካኝነት በጽኑ ተቃውመዋል።

ይህ በመቐለ ከተማ የተጀመረው በበራሪ ወረቀቶች የመቃወም ንቅናቄ የትግራይ ሕዝብ ካለፈው የሁለት ዓመት አስከፊ ጦርነት የተማረውን ትምህርት የሚያሳይ እና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

በከፍተኛ ስጋትና ውጥረት ውስጥ የሚገኙት የክልሉ ነዋሪዎች፥ ዳግም ወደ እልቂትና የደም መፋሰስ የሚወስዱ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደማይቀበሉ በግልጽ እያሳዩ ነው።

የሕዝቡ እምቢተኝነት በትግራይ ክልል ውስጥ ለሰላም ያለውን ከፍተኛ ጉጉት የሚያሳይ ሆኗል።

ሕገ-ወጡ ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ የጦር መሣሪያዎችን እና የሰው ኃይልን መልሶ የማደራጀት ሰፊ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ይፋዊ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

ይህንን ተከትሎም በመቐለና በአካባቢዋ ባሉ ከተሞች የትራንስፖርት መስተጓጎል እና የመንገዶች መዘጋት ክስተቶች የታዩ ሲሆን፥ ይህም በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና እና የደኅንነት ስጋት ደቅኗል።

የመደመር መንግሥት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆን እና ወጣቶች ከግጭት እንዲጠበቁ ሰፊ ጥረቶችን እያደረገ ነው።

የሕገ-ወጡ ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር መመሳጠር፣ ለሀገር ሰላም መደፍረስ እና የሉዓላዊነት መደፈር መነሻ ቢሆንም፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን የሚመርጠው የትግራይ ሕዝብ ድምፅ ግን የቡድኑን የጦርነት ሴራ ለማክሸፍ ትልቅ አቅም እየሆነ ነው።

Exit mobile version