አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትናንትናው ዕለት በቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ተመካካሪዎች ዛሬም በየቡድናቸው በመሆን መመካከር ቀጥለዋል፡፡
50 ተመካካሪዎችን በመያዝ በ80 ቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ንዑሳን ቡድኖች በተሟላ ሁኔታ ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ በየንዑስ ቡድናቸው አስር አስር በመሆን ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሒደት እስከ ነገ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዚህ ሒደት ተመካካሪዎች በሚመካከሩባቸው የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ በርካታ ሃሳቦችን እና ምልከታዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሒደቱ ተመካካሪዎች ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ አመለካከቶችን እና ምክንያቶችን ከስር መሰረቱ አንዳቸው ሌላቸውን እንዲረዱ መደላድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡
ይህንን ሒደት ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት በሙያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እና ለአጀንዳ ሃሳቦቹ ባላቸው ሙያዊ ቅርበት ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸው 80 የሚጠጉ የባለሙያዎች ስብስብ (Panel of Experts) በማሰባሰብ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እያሳተፈ ይገኛል፡፡
የባለሙያዎች ስብስብ በአጀንዳ ነጥቦች ላይ ለሚፈጠሩ ብዥታዎች ማብራሪያ በመስጠት ሒደቱን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል በዚህ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ተቋማት ሒደቱን ለመታዘብ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ባቀረቡት መሰረት ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት፣ ከተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተውጣጡ ከ50 በላይ ገለልተኛ ታዛቢዎች የምክክር ሒደቱን እየታዘቡ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም

