Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ የተረጋጋችና አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር መገንባት ያስችላል – ምሁራን

‎አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አለመግባባቶችን በመፍታት የተረጋጋችና አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር መገንባት ያስችላል አሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን።

በዩኒቨርሲቲው የአመራር እና ፖሊሲ ጥናት መምህር ፍሬው አምሳሉ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የሀገር ግንባታ ሂደት የጋራ ማንነትን ከመገንባት፣ የሀገር ባለቤትነትን ከማረጋገጥ እና ታሪካዊ ስህተቶችን ከማረም ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።

የሀገር ግንባታ የሕግ፣ የባሕል እና የፖለቲካ ተቋማትን በማጠናከር ለዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ ሥርዓት መፍጠር እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ሚና የጎላ መሆኑንም አስረድዋል።

ሂደቱ በብዝሃነት እና በአንድነት መካከል ተገቢውን ሚዛን በመጠበቅ የጋራ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጠናከር እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አስተዳደር መምህር በዳሳ ፍራጃ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ መሆኗን ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ ችግሮችን በምክክርና በውይይት የመፍታት በጎ ባሕል እንደነበራት አመልክተዋል።

ሂደቱ በሀገሪቱ ያሉ የቆዩ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሳሪያ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ምሁራኑ የምክክር ባሕልን ማሳደግ ለአስተማማኝ ሰላምና ለልማት ስኬት አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ምክክሩ የዜጎችን ድምፅ በማድመጥ በፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተዳደር ውስጥ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል የሚፈጥሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች በስምንት ዋና ዋና አጀንዳ ለይቶ በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።

በተስፋሁን ከበደ

Exit mobile version