አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እየተተገበረ ካለው የመደመር እሳቤ ውስጥ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አንዱ ነው፡፡ የሌማት ትሩፋት የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ በመቀየር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንጸባራቂ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በሁሉም የልማት መስኮች ባስመዘገበቻቸው ሁለንተናዊ እመርታዎች መካከል የእንስሳት ሀብት ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይም በእንቁላል ምርት በኩል የታየው ፈጣን ዕድገት የዚህ አገራዊ ንቅናቄ ፍሬያማነት ማሳያ ነው።
አጠቃላይ የግብርና ምርት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን በዚህ ዘርፈ ብዙ አብዮት ውስጥ በእንቁላል ምርት ላይ የታየው አስደማሚ እምርታ ጎልቶ ይጠቀሳል።
አሁን ላይ ዓመታዊ የእንቁላል ምርት 9 ነጥብ 4 ቢሊየን የደረሰ ሲሆን ይህም በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊየን የእንቁላል ምርት አንጻር ሲታይ በሶስት ዕጥፍ አድጓል።
መንግሥት ባደረገው የግብዓት አቅርቦት እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ የአንድ ቀን ጫጩቶች ለህብረተሰቡ እንዲሰራጩ ያደረገ ሲሆን በዶሮ እርባታ ቀደም ሲል የነበረው 26 ሚሊየን የነበረው የጫጩት ሥርጭት ወደ 184 ሚሊየን በማሳደግ ለምርታማነቱ መጨመር ወሳኝ ድርሻ አበርክቷል።
በዋናነት በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ውስጥ ተካትቶ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ የዶሮ እና እንቁላል ምርት ልማት በክልሎች ደረጃ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ በእያንዳንዱ አባወራ ቤት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።
በዶሮ እርባታና በሁለንተናዊ የእንስሳት ልማት የሚከናወኑ ሥራዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና ከፍተኛ ገቢ ለማስገኘት ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረው ነበር።
እንዲሁም አርሶ አደሩ በጓሮው የሚያመርተው እንቁላል፣ ወተትና አትክልት ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና ለኑሮው መሻሻል መሠረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረል።
በመደመር ዕሴትና በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር እየተመዘገበ ያለው የእንቁላልና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ዕድገት የዜጎችን የሥነ ምግብ ደረጃ ከማሻሻል አልፎ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ይህ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚተገበር ጥረት ኢትዮጵያን ከልመናና ድህነት ታሪክ አውጥቶ ወደ ከፍታና ብልጽግና የሚያሸጋግር አስተማማኝ ሀገራዊ መሠረት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በዮናስ ጌትነት

