Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህገ ወጡ ህወሓት በትግራይ ክልል መኖር የማያስችል ሥርዓት አልበኝነት ፈጥሯል – አቶ ሀፍቱ ኪሮስ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል መኖር የማያስችል ሥርዓት አልበኝነት ፈጥሯል አሉ የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት ሀፍቱ ኪሮስ።

አቶ ሀፍቱ እንዳሉት ÷በአሁኑ ወቅት ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የክልሉን ወጣቶች ለሌላ አሳልፎ መሸጥን ጨምሮ የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በማካሄድ ከፍተኛ ግፍና መከራ እያደረሰ ነው፡፡

በክልሉ ህግና ሥርዓት በመፍረሱ ምክንያት የሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ለአደጋ መጋለጡን አንስተው÷ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የትግራይ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት እንዲያገኝና ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማስቻሉን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የክልሉን ሕዝብ አደጋ ላይ እየጣለ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም ስምምነቱን በማፍረስና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ መፈንቅለ መንግሥት በማካሄድ ህገ ወጥ ድርጊቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ይህ ህገ ወጥ ቡድን በፈጠረው ሥርዓት አልበኝነት በክልሉ ወጣቶች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት እየፈጸመና በግዳጅ አፈሳ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሕዝቡን ሰላም እና መረጋጋት ለመመለስ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሊተገበር እንደሚገባም አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ የሚስተዋለው አፈሳ እና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት ወጣቶች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ በተደራጀ መንገድ የራሱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር መቆም እንዳለበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ መልክ መያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን በክልሉ እየፈጠረ ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሕዝቡ በራሱ አቅም ተደራጅቶ ሰላሙንና ደኅንነቱን ማስጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

ህገ ወጥ ቡድኑ እየፈጠረ ያለው ቀውስ በአፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት እንዳለበትና የፌዴራል መንግሥትም በክልሉ ሕግና ሥርዓትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version