አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ያልሄድንበት እና ያልሞከርነው አዲስ መንገድ ነው አሉ በምክክር ጉባዔው እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ኢትዮጵያ ለዘመናት የምትታወቀውና መገለጫዋ የሆነው የጦርነት አዙሪት ለድህነት እና ኋላቀርነት እንደዳረጋት ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
የኢዜማ ተወካይ አርክቴክት ዮሃንስ መኮንን ÷ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ ቢሆንም በወቅቱ የነበሩት ገዥዎች በመቃብራችን ላይ ነው ምክክር የሚደረገው በማለት አሻፈኝ እንዳሉ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎቱን የሚያንጸባርቅበትና ልዩነትን ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ እድል ማግኘቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀደመ መሻት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለዘመናት ልዩነቶችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ዝንባሌ ባህል ከመሆኑም በላይ አውዳሚ እና ትውልድ አምካኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል
ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ያልሄድንበት እና ያልሞከርነው አዲስ መንገድ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር መረባረባቸው አስደሳች መሆኑን ነው ያወሱት፡፡
ይህ እድል ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ልታገኘው የማትችለው በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በመወከል በምክክር ጉበዔው እየተሳተፉ የሚገኙት ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው÷ እንደ ሀገር በምክክር ልዩነቶችን ለመፍታት ብዙ ትግል መደረጉን አንስተዋል፡፡
የፖለቲካ ፍላጎትንና ልዩነትን በጦርነት ለመፍታትመሞከር እጅግ አውዳሚ ከመሆኑም በላይ ጦርነት የአንድ ወገንን አሸናፊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ አዙሪት ሆኖ ሀገራችንን አያሌ ዋጋ አስከፍሏል ብለዋል፡፡
በዚህ ዘመን ያሉብንን ተቃርኖዎች ለልጆቻችን ማሻገር አይገባም ያሉት አቶ ተስፋሁን ÷ ይሄን ምዕራፍ በሀገራዊ ምክክሩ ዘግተን ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ልናስረክብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ልዩነቶች በሀሳብ የበላይነት እና በውይይት መፈታት አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም አለን የሚሉት ደግሞ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ሙሉብርሃን ሀይሌ ናቸው፡፡
በተለይም በትግራይ ክልል በጦርነት ፍላጎትን የማስፈጸም ዝንባሌ መኖሩንና ይህም ማሕበረሰቡን ለመከራ መዳረጉን ጠቅሰዋል፡
ሀገራዊ ምክክሩ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችንን የሚያስቀር፣ ችግር ፈጣሪዎችን ወደ ጎን የሚገፋ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጎለበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሒደት ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የማሕበረሰብ ተወካይ ሀሳብ በመሰንዘርና በከፍተኛ መደማመጥና መከባባር እየተካሄደ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ነዋይ

