አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በጁብሊ ሀውስ በሁለትዮሽ እና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ከአፍሪካ ኅብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባዔ በተጓዳኝ፣ ከጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በጁብሊ ሀውስ በሁለትዮሽና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ከፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ ጀምሮ ለዘለቀው ታሪካዊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷ ትልቅ ሥፍራ ትሰጣለች ነው ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የጋና ኤምባሲ ሕንፃ መጠናቀቅም የሁለቱ ሀገራት የማይናወጥ ወዳጅነት ምልክት መሆኑ በውይይቱ መነሳቱን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ማሃማ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነትና የአንድነት አርማነቷን እንደጠበቀች፣ አሁን ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎች የልማት ዘርፎች እያስመዘገበቻቸው ባሉ አበረታች ለውጦችና ስኬቶች በእጅጉ መደነቃቸውን ገልጸውልኛል ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የጣና ፎረም ለማዘጋጀት እያከናወነች ያለው የቅድመ ዝግጅት ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በፎረሙ ቦርድ ላይ እያበረከቱ ላሉት እጅግ የላቀ አመራርም የከበረ ምስጋናችንን አቅርበንላቸዋል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፡፡

