Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገራዊ ምክክር፣ እጣ ፈንታን የሚቀይር እድል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሺህ ዓመታት ታሪኳ በአንድነት በቆሙ ህዝቦቿ በርካታ አኩሪ ድሎችን ተቀዳጅታለች፡፡

የየራሳቸው ውብ ማንነት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ነጻነትና ክብሯን አስጠብቃ እስከ ዛሬ ዘልቃለች፡፡

እነዚህ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው አስተዳደራዊ፣ የልማትና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ሊኖሯቸው ይችላል፡፡

ለረጅም ዓመታት በፖለቲካ፣ በማንነት፣ በታሪክ ትርጓሜ እና በልማት አቅጣጫ ዙሪያ የተከማቹ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የተጀመረው ብሔራዊ ምክክርም የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ሊቀይር የሚችል ወሳኝ እድል ተደርጎ ይታያል።

ሀገራችን የምትፈልገው ከግጭት ይልቅ ውይይት፣ ከመለያየት ይልቅ መግባባት፣ ከመከፋፈል ይልቅ የጋራ መፍትሄ ነው።

ምክክር በራሱ መዳረሻ አይደለም፤ ይልቁንም ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ ከምክክሩ በኋላ የሚመጡ ተግባራዊ ለውጦች ናቸው።

ከብሔራዊ ምክክር ከሚጠበቁ ዋና ዋና ውጤቶች መካከል በመንግሥት፣ በፖለቲካ ተዋናዮች፣ በማኅበረሰቦችና በዜጎች መካከል የመተማመን መንፈስን ማጠናከር ተጠቃሽ ነው።

ምክክር በሰከነ መንገድ በመወያየትና እርስ በርስ በመደማመጥ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ የዘላቂ ሰላም መሠረት ይፈጥራል።

በሀሳብ ልዩነት ምክንያት ከመጋጨት ይልቅ በውይይት መፍትሔ የመፈለግ ባህል ከተጠናከረ፣ የውስጥ ችግርን ተወያይቶና ተመካክሮ የመፍታት አቅም እንዲሁም የሀገራችን ፖለቲካዊ ሥርዓት የበለጠ እየጠነከረ እንዲመጣ ያግዛል፡፡

ይህም ወደፊት በሚካሄዱ ምርጫዎች፣ የፖሊሲ ውይይቶችና በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ የበለጠ የመግባባትና የመተባበር ባህል እንዲዳብር ይረዳል፡፡

ምክክሩ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት በኩል የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ጠንካራ ተቋማት ሲፈጠሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ሀገር የመገንባትና ልማት የመስፋፋቱ ጉዳይ አይቀሬ ነው፡፡

በተጨማሪም ዘላቂ ሰላም እና የፖለቲካ መረጋጋት ከተጠናከሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይበረታታል፤ የሥራ ዕድሎች በስፋት ይፈጠራሉ፤ የቱሪዝምና የንግድ ዘርፎች እድገትም በዚያው ልክ ይጨምራል።

የተስማማንባቸውን ጉዳዮች በተግባር መተርጎም፣ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ማሳደግ፣ ግልጽነትን ማረጋገጥና ለውጦቹን በተቋማዊ መንገድ ማስቀጠልና ማስፈጸም አስፈላጊ ይሆናል።

ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሊከፍት የሚችል እድል በሆንም ይህ እድል ግን የሚሳካው በተሳታፊዎች፤ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ኃይሎች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ፣ በሚዲያ እና በመላው ዜጎች የቅንጅት ስራ ነው።

ብሔራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version