Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቀይ ቦኔት ክብር የገባው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ ለማስቀጠል፣ የሕዝቦቿን ሰላማዊ ኑሮ በዘላቂነት ለማረጋገጥና በሚከሰቱ ማናቸውም የፀጥታ ስጋቶች ላይ ፈጣንና በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የተገነባ፣ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የታነፀና ለሀገር ፍቅር የቆመ መከላከያ ኃይል ያስፈልጋል።

በዚህ ረገድ በመደመር መንግሥት የሪፎርም ስራዎች ትኩረት ከተሰጣቸውና ከፍተኛ ውጤት ከታየባቸው ተቋማት መካከል የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይገኝበታል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዋቅር ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚይዘው ስፍራ ከፍተኛ ሲሆን፤ ዕዙ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለሕዝብ ደህንነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት የተሰጠውን ሀገራዊ አደራ በብቃት ለመወጣት የተዘጋጀ እና በከፍተኛ ወታደራዊ ብቃት የታነፀ የሠራዊቱ ልዩ ክንፍ ነው።

ዕዙ በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ በላቀ የአካልና የሥነ ልቦና ዝግጁነት እንዲሁም በዘመናዊ የውጊያ ስልቶች የተገነባ የሰው ኃይል በማፍራቱ ሀገር በገባችበት የፈተና ወቅት ሁሉ ውጤታማና አሸናፊ ምላሽ በመስጠት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታን ያተረፈ ኃይል ሆኗል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አባላት የሚያልፉት የስልጠና ሂደት በመደበኛ የውጊያ ጥበብና በአካላዊ ብቃት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን ይልቁንም ዘመናዊ የፀጥታ ስጋቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ውስብስብ የውጊያ ስልቶች ፈጣን ውሳኔ የመስጠት ብቃት፣ የአመራር ችሎታና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በጥልቀት አካትቷል።

አባላቱ በከባድ የተፈጥሮ መሬት አቀማመጦች፣ በአስቸጋሪ የአየር ጠባዮች እና ከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት በሚፈጥሩ ድንገተኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይበገሩ ፈጣንና ትክክለኛ ርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸውን ጠንካራ ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙ ሲሆን፤ ይህም በማንኛውም ግዳጅ ላይ በላቀ ብቃት እንዲወጡ ያስችላቸዋል።

በተጨማሪም ዕዙ በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በላቁ የክትትል ድሮኖች፣ በዘመናዊ የመገናኛ ሥርዓቶችና በሌሎች ቴክኖሎጂያዊ አቅሞች የተደገፈ በመሆኑ፣ በውጊያ ሜዳ የመረጃ የበላይነትንና የውሳኔ ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል።

የዕዙን ወታደራዊ ዝግጁነት በየብስ፣ በተራራና በወንዞች ላይ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ባለፈ፣ ወደ ባሕር ኦፕሬሽኖችም በማስፋት በባሕር ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከልና የወንድማማች ሕዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም እንዲኖረው አድርጎታል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ስለ ዕዙ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ የሽብር ስጋቶችን ለመመከት፣ ወንድማማች ሕዝቦችን ለመደገፍና በቀጣናው ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቂ አቅም ያለው ኤሊት ፎርስ መገንባቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዕዙ አባላት የቀይ ቦኔት ክብር የገባቸው፣ ለሀገር ሰንደቅ ዓላማና ለነፃነት ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ የሀገር አለኝታዎች መሆናቸውን በመግለጽ ዕዙ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በብቃት የሚጠቀምና ከብሔርና ከፖለቲካ ውግንና ነፃ ሆኖ ሀገርን የማጽናት አደራ የተቀበለ ተቋም መሆኑንም አስታውቀዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደሚገልጹት፤ ሠራዊቱ ባለፉት ዓመታት ከውስጥና ከውጭ የተቃጣበትን የውክልና ጦርነት በብቃት በመመከት ታሪካዊ ገድሎችን የፈጸመ ሲሆን፣ የሪፐብሊካን ጋርድን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትን ያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በየብስ፣ በአየርና በባሕር የሚሰጡ ግዳጆችን በብቃት ለመፈጸም የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ አቅም የገነባ ሲሆን በማንኛውም ሁኔታ ተልዕኮውን በስኬት ለመወጣት በሙሉ ዝግጁነት ላይ ይገኛል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር፣ የሕዝብን ሰላም የሚያስጠብቅ እና በቀጣናው የሚከሰቱ የፀጥታ ስጋቶችን በብቃት የሚመክት የጀግንነትና የጽናት ተቋም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በዘመናዊ ትጥቅ፣ በላቀ ስልጠና፣ በከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ ምግባርና በጠንካራ የሀገር ፍቅር መንፈስ የተገነባው ይህ የሠራዊቱ ክንፍ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማትና የወደፊት ተስፋ ለማስጠበቅ የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version