በአሁኑ የጂኦፖለቲካና የቴክኖሎጂ ዘመን፣ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በምድር፣ በባህርና በአየር ላይ በሚደረግ መደበኛ ጥበቃ ብቻ አይደለም።
የሳይበር ምህዳር የጦር ግንባር እየሆነ በመምጣቱ፣ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነቷንና ጥቅሟን ለማስጠበቅ ወደ ዲጂታል አብዮት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
ይህ የዲጂታል አብዮት የሀገሪቱን ወሳኝ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ ብሔራዊ መረጃዎችንና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞችን ከሳይበር ጥቃቶችና ከዲጂታል ጣልቃ ገብነቶች ለመከላከል የተነደፈ ስትራቴጂያዊ ጋሻ ነው።
በመሆኑም የቴክኖሎጂ አቅምን መገንባትና የሳይበር ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ የህልውና እና የሉዓላዊነት መገለጫ እየሆነ መጥቷል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የዲጂታል አብዮት የሀገሪቱን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ከመቀየር ባለፈ፣ የፀጥታና የደህንነት ተቋማትን የአሰራር መዋቅር በከፍተኛ ሁኔታ እያዘመነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሰራሮቻቸውን ወደ መረጃ መር እና በቴክኖሎጂ ወደታገዘ ዘመናዊ መዋቅር ቀይረዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል 2025ን ሙሉ በሙሉ አሳክታ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጉዞዋን ጀምራለች፡፡ የዲጂታል ሽግግሩ በፀጥታው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱን ወሳኝ መሰረተ ልማቶች እንደ ባንኮች፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም አውታሮች ከባዕድ የሳይበር ጥቃቶች የመጠበቅ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
ተቋሙ የሀገር ውስጥ የሳይበር ደህንነት ምርቶችን እና ሶፍትዌሮችን በራስ አቅም በማልማት ጥገኝነትን ቀንሷል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የቪዲዮ ክትትል መረጃዎችን በራስ-ሰር የሚተነትኑ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ አድርጓል።
ይህም በዋና ዋና ከተሞች የፊት እና የሰሌዳ መለየት ስራን በማቃለል ወንጀልን የመከላከል አቅምን ጨምሯል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የዲጂታል ሲስተሞችን እና የኢ-ፓስፖርት አሰራርን በማስፋፋት የድንበር ቁጥጥርን አጥብቋል። ይህም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የሰነድ ማጭበርበርን ለመግታት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ከጸጥታ መረጃዎች ጋር መተሳሰሩ የፋይናንስ ወንጀሎችን፣ የገንዘብ ማጠብን እና ለሽብርተኝነት የሚሆን የገንዘብ ዝውውርን በቀላሉ ለመከታተል አስችሏል።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት የዲጂታል አብዮቱን በበላይነት ለመምራት እና ሀገራዊ ደህንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ወሳኝ ስትራቴጂዎችን እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህም በሳይበር ደህንነት እና በዲጂታል ፎረንሲክ ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ተችሏል፡፡ የሳይበር ወንጀልን፣ የመረጃ ደህንነትን እና የዜጎችን የግል መረጃ ጥበቃ የሚደነግጉ ህጎችም በየጊዜው እየተሻሻሉ ነው፡፡
በውጭ ሀገራት ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚኖረውን ጥገኝነት ለመቀነስ የሀገር ውስጥ የሶፍትዌር ባለሙያዎችን እና የፈጠራ ስራዎችን እያበዙ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል አብዮት የሀገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አኳያ ወሳኝና የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ሀገሪቱ እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባሉ ተቋማት አማካኝነት የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል፣ የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት የመግታትና የወንጀል መከላከል አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋለች።
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በማበልጸግ በራስ አቅም መተማመን ላይ ያተኮረ ጉዞ ላይ ናት። በመሆኑም ዲጂታላይዜሽን ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሉዓላዊነቷን አስከብራ እንድትቀጥል የሚያስችላት ዋነኛ ብሔራዊ ዋስትናዋ ነው።

