Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገራዊ ምክክሩ የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ሰላምና ልማትን ያረጋግጣል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ሰላምና ልማትን ያረጋግጣል አሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል።
ምክክሩ አጀንዳዎችን በማብላላትና በምሁራን ገለጻዎች ተደግፎ በስኬት እየተካሄደ ሲሆን፤ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች በቡድን ተከፋፍለው የተሰጧቸውን አጀንዳዎች በትክክል በማብላላት፥ በመደማመጥና በመከባበር ወደ ሀሳብ ማጠናቀር ሂደት ተሸጋግረዋል።
በሂደቱ ተሳታፊዎች እርስ በርስ እንዲቀራረቡና አጀንዳዎችን በጥራት እንዲያበላሉ በተዘረጋው አሰራር መሰረት ውጤታማ ስራ ተከናውኗል።
የምክክሩን ሂደት አስመልክቶ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ያደሩ ቁርሾዎችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል።
ከሁሉም አካባቢዎች የተነሱ ጥያቄዎች ከሁሉም አካባቢዎች በተወከሉ ተመካካሪዎች የጋራ መግባባት እንደሚፈጠርባቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።
ታሪካዊ በሆነው ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች እና ባለቤቶች በመሆናችን ደስታ ይሰማናል ነው ያሉት፡፡
‎ለአፍሪካ ምሳሌ የምትሆን ሀገር ለመገንባት አንድነትን ማጠናከር እና ውይይት ወሳኝ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች ሀገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲሁም ልማቱን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ተስፋ እናደርጋለንም ነው ያሉት።
‌‎
በኦሊያድ አህመድ

Exit mobile version