በአፍሪካ ሀገራት ያጋጠሟቸውን ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና የእርስ በርስ ግጭት ቀውሶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ ምክክርን እንደ ዋና መፍትሔ ተጠቅመዋል።
ያካሄዷቸው ምክክሮች ሀገራቱ ወደ ከፋ እልቂትና መበታተን እንዳይገቡ በመታደግ አዲስ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ለምሳሌ ያህል የደቡብ አፍሪካ፣ የቱኒዚያ፣ የሩዋንዳ፣ የኬኒያን እና የናይጄሪያን ተሞክሮ እንመልከት፡፡
በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር በተደረገው የኮዴሳ የድርድርና የምክክር መድረክ ሀገሪቷ ከመበታተን ልትድን ችላለች፡፡ በወቅቱ የኔልሰን ማንዴላ እና የኤፍ ደብሊው ዲክለርክ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሀገሪቱን ከከፋ የዘርና የእርስ በርስ ደም መፋሰስ ታድጓታል። በምክክሩ አማካኝነት አዲስ ሕገ-መንግሥት ተቀርጾ ሁሉንም ያካተተ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል።
ቱኒዚያ በፈረንጆቹ 2011 ከተቀሰቀሰው የዓረብ ጸደይ አብዮት ማግስት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስና የእርስ በእርስ ጦርነት አፋፍ ደርሳ ነበር። ነገር ግን የሠራተኛ ማኅበራት፣ የንግድ ምክር ቤትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ያቀፈው የቱኒዚያ ብሔራዊ የምክክር ኳርት የፖለቲካ ኃይሎችን ወደ ጠረጴዛ አምጥቷል። ይህ የጋራ የምክክር ስኬት ሀገሪቱን ከጥፋት በመታደጉ ስብስቡ በፈረንጆቹ 2015 የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲያገኝ አስችሎታል።
ሩዋንዳ በፈረንጆቹ 1994 ከተከሰተው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል በኋላ ማኅበራዊ ትስስሯን ለመጠገንና ብሔራዊ እርቅ ለማውረድ የውስጥ የምክክር መድረኮችን ተጠቅማለች። በዚህ ሂደት ውስጥም የሀገር በቀል እውቀቶች ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ጋቻቻ የተሰኘውን የሀገር በቀል ባህላዊ የውይይትና የፍትሕ ሥርዓት (የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች) በመጠቀም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጉዳይ በማየት ማኅበረሰባዊ እርቅና አንድነትን መፍጠር ችለዋል።
ኬንያ በፈረንጆቹ ከ2007-2008 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማግስት የተነሳውንና የሰዎችን ሕይወት ያጠፋውን ከባድ ግጭት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር አካሂዳለች። በወቅቱ በነበሩት ተቀናቃኝ መሪዎች ምዋይ ኪባኪ እና ራይላ ኦዲንጋ መካከል በተደረገው ብሔራዊ ውይይት ስምምነት ተደርጎ ሰላም ወርዷል።
ናይጄሪያ ከታሪካዊው የቢያፍራ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ “አሸናፊም ተሸናፊም የለም” የሚል ፍልስፍናን በመከተል ብሔራዊ መግባባት ላይ ሰርታለች። መሣሪያ አንስተው የነበሩ ወገኖችን እንደ ጠላት ሳይሆን መንገድ እንደሳተ ቤተሰብ በመቁጠር ወደ ማኅበረሰቡና ወደ ብሔራዊ ጦር ሠራዊቱ በማካተት ሀገሪቱን ከመበታተን ታድገዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ለአራት ዓመታት ያህል ባደረገው ዝግጅት ከአራት ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያቀፈ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ሂደትም የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ በሚለው መርህ የቆዩ ልዩነቶቻችን ይፈታል፡፡

