የኢትዮጵያ የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካ ማዕከልነት፣ ከዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡
እነዚህ ሁለት አበይት የውኃ አካላት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት፣ የደኅንነት ዋስትና እና የሀገር ሉዓላዊነት መሠረቶች ናቸው፡፡
የዓባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ የልማት፣ የሀብት እና የህልውና ምንጭ እንደሆነው ሁሉ፤ የባህር በርም የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት መሠረት ነው።
የኢትዮጵያውያን የትውልድ ቅብብሎሽ ህልም የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የውኃ ኃይል ተጠቃሚነት አረጋግጧል፡፡
ግድቡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በጎረቤት ሀገራት መካከል የኃይል ትስስር በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ያለምንም ጉዳት፣ በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀምና የመልማት መብቷን እያረጋገጠች ትገኛለች፡፡
የዓባይ ውኃ ለኢትዮጵያ ልማት ወሳኝ እንደሆነው ሁሉ፣ የቀይ ባሕርም ለባሕር በር እና ለዓለም አቀፍ የንግድ መስተጋብር በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የንግድ መስመር ያላት ተደራሽነት ለቀጣናው ሰላምና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የቀይ ባሕርን ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ ከሀገሪቱ የባህር በር ፍላጎት እና ከቀጣናዊ ፀጥታ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡
ከዓባይ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ጎን ለጎን፣ የቀይ ባሕር የወደብ ባለቤትነት ለቀጣናዊ ሰላም፣ ለኢትዮጵያ የወጪና የውስጥ ንግድ እንቅስቃሴ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የነበራትን እንጉርጉሮና የዘመናት ቁጭት በሕዳሴው ግድብ ስኬት ቋጭታለች፡፡ የቀይ ባሕርም በቅርቡ ምላሽ የሚያገኝ አይቀሬው የውኃ አጀንዳችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህልውና ከሁለቱ ውኃዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ እነዚህን የውኃ ሀብቶች በዘላቂነት ማልማትና ከቀጣናዊ ተደራሽነት ጋር ማስተሳሰር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ነው።

