Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ቱሪዝምን ያጠናክራል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት የቱሪዝም ስራችንን ያጠናክራል አሉ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ ምክክር ተካሂዷል።

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በምክክር መድረኩ እንደገለጹት፤ ክልሉ ካለው እምቅ የቱሪዝም ጸጋ አንጻር ዘርፉን ማልማት እና ማስተዋወቅ ላይ ማተኮር ይገባል።

አሁን ያለንበት ጊዜ ለጥናትና ምርምር ስራ ምቹ መሆኑን ተከትሎ የጂኦ ፓርክ የጥናት ውጤት ለክልሉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው ጥረት የቱሪዝም ስራችንን ያጠናክራል ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃት የመረጃ ማዕከላትን ማጠናከር እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት የኢኮኖሚ አቅሙን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ምሁራን እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመረው ጥረት ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና ለነበራቸው አካላት ምስጋና ቀርቧል።

ተካልኝ ኃይሉ

Exit mobile version