አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን በመላው የትግራይ ክልል የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እያካሄደ መሆኑን ተከትሎ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ወጣቶች ወደ መሀል ሀገር ሸሽተዋል፡፡
ሕገወጡ ቡድን በክልሉ ውስጥ በርካታ አፋኝ እና ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ሕጎችን አውጥቶ እንቅስቃሴውን የሚቃወሙትን እያሰረ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል በሰሜን ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ጦርነት ወቅት በትግራይ ቴሌቪዥን ዋነኛ ዜና አቅራቢ የነበሩት ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ በክልሉ በሚዲያ ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል፡፡
በዚህም የሕገወጥ ቡድኑን አሰራር እና በስተጀርባ ያሉ እውነታዎችን ጠንቅቀው ለማወቅ መቻላቸውን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ፣ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አንድ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም። ህዝቡ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላም መኖር የሚፈልግ ቢሆንም ቡድኑ ግን ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ህዝቡን ታጋች አድርጎታል” በማለት ሁኔታውን ያብራራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የህዝቡን መከራ ለማስቆም እና ሰላም እንዲያገኝ ድምፅ ለመሆን መቁረጣቸውን የሚናገሩት ጋዜጠኛው፤ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የህዝቡን የሰላም ጥማት እና የሕገ ወጡ ቡድን የሚከተለውን አጥፍቶ የመጥፋት አካሄድ ፍጹም አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል ይላሉ።
የፌደራል መንግሥት ችግሮችን በምክክር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሩ ክፍት ቢሆንም፤ በአንጻሩ የህገ ወጡ ቡድን አመራሮች የሰላም አማራጭን በመተው ግልፅ የጦርነት ድቤ እየደለቁ ይገኛሉ ብለዋል።
ቡድኑ ከጦርነት ይልቅ የህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ እና ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄዎችን አብዝቶ እንደሚፈራ፤ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቹ ጋር በሰላም መኖር የሚፈልግ ቢሆንም፣ ቡድኑ ግን ህዝቡን ታጋች በማድረግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ጋዜጠኛው ይገልፃሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አንድ እንዳልሆኑና ሊሆኑም እንደማይችሉ የሚያነሱት ጋዜጠኛው ቡድኑ የራሱን ውድቀት ለመሸፈን ሲል የትግራይን ህዝብ ለከፋ አደጋ በማጋለጥ ከፌደራል ስርዓቱ ለመነጠል እና በህዝቦች መካከል የጥርጣሬ ግንብ ለመገንባት እያሴረ ይገኛል ነው ያሉት።
የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት እና ሕገ መንግ|ቱን በግልፅ የጣሰ ተግባር ላይ በመሰማራት ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች እና ቀጣናውን ከሚያተራምሱ ኃይሎች ጋር «ስትራቴጂካዊ ጥምረት» ፈጥሬያለሁ ማለቱ የተስፋ መቁረጥ ጫፍ ማሳያ ነው።
የሻዕቢያና የግብፅ አሽከር በመሆን የሀገርን ሉዓላዊነትና ደህንነት አደጋ ላይ መጣል የታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል መሆኑን ጋዜጠኛው ያስረዳሉ።
ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስ የሚደረገው ጥረት ታሪካዊ የሀገር መክዳት ወንጀልና በህዝብ ላይ የተፈፀመ ከፍተኛ ስብራት እንደሆነም አብራርተዋል።
ትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት ሰላሟን አጥታለች፤ ትምህርት፣ ጤና እና የልማት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መቆማቸውን ነው ያነሱት።
ቡድኑ የ70 እና የ80 ዓመት እናቶችን እያሰቃየ፣ ወጣቱን ደግሞ በግዳጅ አፈሳ ወደ ጦርነት እያጋዘ ሲሆን የትግራይ ወጣት የቡድኑን የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠር ብር እየከፈለ ወደ መሀል ሀገር በመጎረፍ ላይ ይገኛል።
ከግማሽ ሚሊየን በላይ ህዝብ ክልሉን ለቆ መውጣቱ ህዝቡ የህወሓትን የጥፋት ውጊያ አጥብቆ መቃወሙን በግልፅ ያሳያል።
በዚህም ምክንያት የትግራይ እናቶች በወሊድ ምክንያት በየቤታቸው የሚሞቱበት፣ ወጣቱ ደግሞ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሊቢያና ሱዳን የሚሰደዱበት አሰቃቂ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተፈጥሯል።
ቡድኑ ህዝቡን ለማዳን ሳይሆን ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ሀገራዊና ቀጠናዊ ስጋት ሆኖ በመቀጠል፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ሀብት የመዝረፍና የወጣቱን ህይወት የመሸጥ እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።
ይህ በክልሉ እየደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ውድቀት አፋጣኝ እልባት ካላገኘ የትግራይን ህዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የፌደራል መንግሥት የትግራይን ህዝብ ከዚህ አጥፍቶ ጠፊ ቡድን ሊታደጉት ይገባል ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በክልሉ ያለውን የህዝብ እንግልት ማስቆም ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበትም ነው የሚያመለክቱት።
በተጨማሪም በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ኤሊቶች እና ወጣቶች ይህንን እውነታ ተረድተው የጦርነትና የጥፋትን ሳይሆን የሰላም፣ የቴክኖሎጂ እና የልማት ጀግና ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የትግራይ ህዝብ በሀገሩ በሰላም የመኖርና የመልማት መብቱ እንዲከበር፣ ህዝቡን ከጠላት ጋር በመሻረክ ከሚሸጡ አመራሮች ወጥቶ ለሰላምና ለአንድነት መቆም ጊዜው አሁን ነው።
በዮናስ ጌትነት

