አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ከሆርቲካልቸር ወጪ ንግድ 490 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የሆርቲካልቸር ወጪ ንግድ አፈፃፀም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ከሆርቲካልቸር ምርቶች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ወደ ውጭ የሚላኩ የዘርፉ ምርቶችን መጠንና ጥራት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአበባ ምርት 412 ሚሊየን ዶላር፣ በአትክልት 57 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም በፍራፍሬ 21 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል፡፡
በ2019 በጀት ዓመት 357 ሺህ 457 ቶን የአበባ፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርት ወደ ውጭ በመላክ 575 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነጋ መኳንንት በበኩላቸው÷ የዘርፉን ወጪ ንግድ ግብ ለማሳካት ለኢንቨስትመንት ምቹ መደላድል መፍጠር ላይ መስራት እንደሚገባ መጠቆማቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

