አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንሳይ እና ስፔን በተከሰተ የሰደድ እሳት ምክንያት ከ220 ሺህ በላይ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።
በፈረንሳይ ቦርዶ አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑ 60 ሺህ ያህል ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
በዚህም በፈረንሳይ እና በስፔን እየተስፋፋ ባለው የሰደድ እሳት አደጋ ከአካባቢያቸው ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ሰዎችን ቁጥር ከ220 ሺህ በላይ አድርጎታል።
በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በርካቶች እንዲወጡ ተደርጓል።
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አደጋውን ለመቆጣጠር ወታደሮችን አሰማርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በማድሪድ አቅራቢያ የተከሰተው የሰድድ እሳት ከባድ በመሆኑ ከአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን የስፔን ባለስልጣናት ጠቁመዋል።
የስፔን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን፤ በአደጋው ምክንያት 25 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲወጡ እንዲሁም 40 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ በቤታቸው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የማድሪድ የክልላዊ ፕሬዚዳንት ኢዛቤል ዲያዝ አዩሶ እንዳሉት፤ የተከሰተው የሰደድ እሳት አደጋ በቀጣናው ታሪክ አስከፊው ነው።
የአካባቢው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሰደድ እሳቱ ከዋና ከተማዋ 50 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀው ወደሚገኙት የሮብሌዶ ዴ ቻቬላ እና ፍሬስኔዲላስ ዴ ላ ኦሊቪያ ማዘጋጃ ቤቶች እየተሸጋገረ ነው።
በአብረሃም አበራ

