Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ8 ሺህ 900 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ተችሏል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በ2018 በጀት ዓመት ከ8 ሺህ 900 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ተችሏል አሉ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5 ዓመት 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ክልሉ በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
በዋናነት የክልሉ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ያረጋገጠ ሲሆን የኢኮኖሚ አቅሙንም ማሳደግ አስችሏል ነው ያሉት።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ55 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አመልክተው የመካናይዜሽን እርሻ ተግባራዊ በመደረጉ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሄክታር እስከ 34 ኩንታል ምርት ማግኝት ተችሏል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ለክልሉ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ዘርፉ ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ በማድረግና አነስተኛ የማዕድን አምራቾችን ወደ ስራ በማስገባት ከ8 ሺህ 900 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል።
በክልሉ ያለውን የልማት ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን ለማድረግም የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በማዘመን የተሻለ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
Exit mobile version