አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ የሚዳስሰው አዲስ መፅሀፍ በዛሬው እለት ተመርቋል፡፡
መፅሀፉ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት ዓፀደወይን(ዶ/ር) የተፃፈ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈባቸውን የታሪክ ውጣ ውረዶች እና ተቋማዊ የለውጥ ጉዞ በሰፊው የሚዳስስ ነው፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ አስራት ዓፀደወይን (ዶ/ር) ÷50 በመቶ የሚሆነው የመፅሀፋ የመጀመሪያ እትም ሽያጭ ለተቸገሩ ህፃናት ተማሪዎች የ2019 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ ሟሟያ እንደሚውል ገልፀዋል።
የተቋማት ታሪክና ጉዞን መሰነድ የተሻለ ነገን ለመገንባት ወሳኝ ነው ያሉት ደራሲው÷መፅሐፉ ታትሞ ለምርቃት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገለፀው፣ለመፅሐፉ ህትመትና ምርቃን አስተዋፅዎ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ÷ መፅሐፉ ዩኒቨርስቲውን ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የከተማውን ማህበረሰብ ጉዞ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።
መፅሃፉን ላበረከቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት ዓፀደወይን(ዶ/ር) እና ቤተሰቦቻቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በነብዩ ዮሐንስ

