Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምድሩም የአየሩም ዘብ – የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትና ዘላቂ ህልውና የሚረጋገጠው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂና የወታደራዊ ስልት በታጠቀ የማይናወጥ የሕዝብ ደህንነት ሰራዊት መገንባት ሲቻል ነው።

የመደመር መንግሥት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ህልውና ደጀን የሆኑ የጸጥታ ተቋማትን ትውልድ ተሻጋሪነት ለማረጋገጥ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ ቁልፍ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በዚህም መሠረት በመከላከያ ሰራዊቱ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር እና የሳይበር ኃይሎች ላይ ቅድሚያ በመስጠት እጅግ ሰፊና ውጤታማ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ወታደራዊ ሪፎርሙ አስፈላጊነት ሲገልጹ፥ ኢትዮጵያን መድፈር ለሚያስቡ ኃይሎች እንደ አባቶቻችን ሀገራችንን ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም የሚፈጠርበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታዲያ ይህ ርዕይ ዛሬ ላይ በተግባር ተተርጉሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው የሚበቃ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ለሀገር ኩራት የሆነ ሰራዊት መገንባት ተችሏል።

ሰራዊቱ ራሱን በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርትና ስልጠና በማነጽ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው የማይናወጥ ጠንካራ የኃይል ሚዛን መፍጠር ችሏል።

በምድርም በአየርም ጊዜውን የዋጀ ኃይል መፍጠር የቻለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፥ በድሮን ቴክኖሎጂ የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመሰለልና መረጃ በመሰብሰብ ረገድ የላቀ ብቃት ገንብቷል።

በተጨማሪም የጠላትን የድንጋይና የኮንክሪት ምሽጎች በቀላሉ ማፍረስ የሚችል የድሮን ቴክኖሎጂዎችን ታጥቋል፡፡

ሰራዊቱ በገነባው ኃይል በምሽግ ውጊያ ላይ ብቻ ሳይወሰን በስትራቴጂያዊ ቦታዎች እንዲሁም በሰላም ወረዳዎች የሚነሱ የጸጥታ ስጋቶችን በፍጥነት በመግባት ውጊያን በአጭር ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቅ ልዩ ብቃት ተላብሷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀና በአግባቡ የሚጠቀም በመሆኑ የጦርነትን ባህሪ ሙሉ በሙሉ በመቀየር ስትራቴጂያዊ የበላይነትን ተጎናጽፏል።

ኢትዮጵያ የጸጥታና የደህንነት ተቋማቷን በዘመናዊ የጦር ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በትጥቅ በማዘመን ማንኛውንም የውስጥና የውጭ የጸጥታ ስጋትን ገና ከጥንስሱ የማምከን ስትራቴጂያዊ ከፍታ ላይ መድረሷን ወዳጆቿም ጠላቶቿም ጠንቅቀው ተረድተውታል፡፡

በሶስና አለማየሁ

 

 

 

Exit mobile version