ኢትዮጵያ እምቅ የውሃ ሀብት እና የለማ መሬት ቢኖራትም፣ ግብርናዋ ለዘመናት በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ለድርቅና ለምግብ ዋስትና እጦት ስትጋለጥ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ይህንን ታሪካዊ ተግዳሮት ለመቀየር በመስኖ ልማት ላይ ሰፊ ሥራ ሰርቷል።
የመስኖ ልማቱም በሀገሪቱ የግብርና ምርታማነት፣ የምግብ ዋስትና እና የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።
በሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ለውጥ ያመጣው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚሊየን የሚቆጠር ሔክታር መሬት በመሸፈን ኢትዮጵያን ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት አሸጋግሯታል።
የመስኖ ልማት ውጤታማነት ትልቁ ማሳያ የበጋ ስንዴ ምርት ሲሆን÷ ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ወጪ አድርጋ ስንዴ ከመግዛት አድኖ ወደ ውጭ መላክ እንድትጀምር አድርጓታል።
አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅትን ሳይጠብቅ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ እንዲያመርት በማስቻል የመሬት አጠቃቀም ውጤታማ እንዲሆንና የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ አስችሏል።
በትላልቅና መካከለኛ ወንዞች ላይ የተገነቡ ዘመናዊ ግድቦችና የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮች ሰፊ የእርሻ መሬቶችን በቋሚነት ማልማት አስችለዋል።
በከርሰ ምድር የውሃ አጠቃቀም ላይ በተሰራው ሥራ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር የውሃ እጥረት ባለባቸውና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ጭምር ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርቱ ተደርጓል።
ባህላዊ የውሃ መሳቢያ ዘዴዎችን በዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ፓምፕ ቴክኖሎጂዎች በመተካት የአርሶ አደሩን ወጪና ድካም መቀነስ ተችሏል።
የውሃ ብክነትን ለመቀነስ እንደ ጠብታ መስኖ እና ረጭ መስኖ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተለመዱ መጥተዋል።
የኩታ ገጠም እርሻ አነስተኛ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በጋራ በማስተሳሰር የመስኖ መሠረተ ልማትን በጋራና በቁጠባ እንዲጠቀሙ አግዟል።
በመስኖ የሚለሙ የአትክልት፣ ፍራፍሬና የቅባት እህሎች ምርቶች ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል አልፈው ለውጭ ገበያ መቅረብ ጀምረዋል።
በገጠርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን÷ ለሀገር ውስጥ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዲኖር አስችሏል።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የመስኖ ልማት እመርታ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ እያፋጠነው ይገኛል።
የተጀመሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ኢትዮጵያ በግብርና ምርታማነቷ ስኬታማ መንገድ ላይ እንደሆነች ማሳያ ናቸው።
ይህ እመርታ የግብርናውን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን መላውን የሀገሪቱን የኢንዱስትሪና የወጪ ንግድ ዘርፍ የሚያግዝ ትልቅ አቅም ሆኗል።

