አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ማሰባሰብ ስኬታማ ሥራዎች ተሰርተዋል አለ።
የሚኒስቴሩ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በወቅቱ እንዳሉት፤ በስርዓታዊና ተቋማዊ ግንባታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ማሰባሰብና የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች መሪነትን ማጠናከር ላይ ስኬታማ ሥራዎች ተሰርተዋል።
በፖሊሲና ስትራቴጂ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና በመተግበር ረገድም ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያ 3ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ ተዘጋጅቶ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግባቱንና በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ስትራቴጂ እንዲሁም የካርበን ገበያ አዋጅ መፅደቃቸውን አስታውሰዋል።
በዘርፉ በዲጂታል መንገድ ተዓማኒ መረጃ ለመሠብሠብ የሚያስችሉ የልኬትና ዘገባ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ወደሀገር ለማምጣት የሚያስችሉ ቁልፍ የሆኑ ፕሮጀክቶች በመቅረፅ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ ከ1 ነጥብ 32 ቢሊየን ዶላር በላይ የፀደቁና በመተግበር ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አሉ ብለዋል።
ከ590 ቢሊየን ዶላር በላይ ሊገኝባቸው የሚችሉ 26 ፕሮጀክቶች ለልማት አጋሮች ተልከው በሂደት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፋዊው የአየር ንብረት መድረኮች ላይ ያላትን ሚና ለማጠናከር በተደረጉ ጥረቶች ሰባት የተለያዩ ኮንፍረንሶችን አስተናግዳለች ነው ያሉት።
በጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት መከላከል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷን እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር እውቅና ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ውጤታማ ሥራዎችን በማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም በ2019 በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በአንዷለም ተስፋዬ

