አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃ ሃብትን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እየተሰራ ነው አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፡፡
የውሃ ሀብትን በተቀናጀ መንገድ ለማልማት፣ ለማስተዳደርና በቀጣይነት ለመጠቀም በሚያስችለው የተፋሰስ ም/ቤት ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የተፋሰሶች ከፍተኛ ም/ቤት አዋጅ ከጸደቀ በኋላ የአዋጁን ድንጋጌዎች ለመተግበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የውሃ ሃብት በሳይንሳዊ መሠረትና በተቀናጀ አስተዳደር ሲመራ ለልማት፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለኢነርጂ ምርት፣ ለኢንዱስትሪና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡
የረቂቅ ደንቡ ጥራት በባለድርሻ አካላት በሚቀርቡ ገንቢ ሀሳቦች እና አስተያየቶች እንደሚጠናከር አመልክተዋል፡፡
አዋጁ የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እንደሚያስችል ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
በተጨማሪም ከአየር ንብረት ለውጥ የሚመነጩ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም፣ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመቀነስና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተቀናጀ ሁኔታ ለማጠናከር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
አዋጁ በዋናነት የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ፣ የተፋሰስ መረጃ ሥርዓት ማቋቋም፣ የውሃ ሀብት ምደባና አጠቃቀምን በፍትሃዊነት መምራት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

