Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሰራዊቱ ለሀገሩ በጀግንነት ከመቆም ባለፈ በልማት ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ከመቆም ባለፈ በልማትና በጎ ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አሉ የምስራቅ እዝ ም/አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜ/ጄነራል ተስፋዬ ረጋሳ።

የምስራቅና የሰሜን ምዕራብ እዞች ከፍተኛ አመራሮችና የሰራዊቱ አባላት በባሕር ዳር መኮድ ካምፕ በመገኘት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አከናውነዋል።

ሜ/ጄ ተስፋዬ ረጋሳ በዚህ ወቅት÷ የሀገር ፍቅርን በተግባር እያሳየ የሚገኘው ሰራዊታችን፣ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ የተጣለበትን አደራ በላቀ ብቃትና ጀግንነት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪዎችና ከውስጥ የጥፋት ሃይሎች በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ለአካባቢ ጥበቃና ለሕዝብ ተጠቃሚነት በሚሰሩ የልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ዛሬ የተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም የዚሁ ልማታዊ አቋም ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመው÷ ችግኝ መትከል ሰላምን ከማወጅ፣ ለም አካባቢን ከመፍጠርና የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ከማብሰር ጋር ተያያዥነት እንዳለው አስረድተዋል።

“ሰራዊታችን ሁልጊዜም ለሰላምና ለልማት ዝግጁ ነው” ያሉት ሜ/ጄነራሉ÷ በቀጣይም ከሀገር አደራ ጎን ለጎን የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Exit mobile version