አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫና የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ ነው አሉ የምክክር ጉባዔው ተሳታፊዎች፡፡
የጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን እንዳሉት÷ ምክክሩ አንዱ የሌላውን ፍላጎት እና አተያይ በአግባቡ እንዲረዳ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ጉባዔው ዜጎች ፍላጎታቸውን ማስረዳትና የሌሎችን ሀሳብ መስማት የሚችሉበት እንዲሁም ለሀገር ግንባታ ገንቢና ጠቃሚ ሀሳቦች የሚነሱበት በኢትዮጵያ አዲስ ባህልና ልምምድ መሆኑን ገልጸዋል።
በዜጎች መካከል መተማመንን መፍጠር የሚያስችል አሳታፊ እና አካታች ጉባዔ በመሆኑ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛው ተሳታፊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ÷ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ለዘመናት የቆዩና ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ርምጃና ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኅብረቱ ከ10 በላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት በጉባዔው የብዙሃን ማኅበረሰብ ተወካዮች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ሀሳብ ሲያንሸራሽሩ መታዘቡን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በቋንቋቸው በነጻነት መግለጽና ማዳመጥ የሚችሉበት አስተርጓሚዎችን ማሰማራቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የተመካካሪዎች ንቁ ተሳትፎ በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ ፖለቲካዊ መግባባት በመፍጠር ተቋማዊ መፍትሔ ለማመንጨት የጎላ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።
በምክክር ጉባዔው ተሳትፎው የተለያዩ ልምድና ተሞክሮ ማግኘቱን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ዮሴፍ አበራ ነው፡፡
በምክክር ጉባዔው የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ሀሳቦች እየመነጩ መሆኑንና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል ስኬት እንደሚመዘገብ አስረድቷል፡፡

