ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩናይትድ ኪንግደም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አረጋገጡ።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ወደ ብሪታንያ አቅንተው አዲስ ከተሾሙት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ጋር ዛሬ ይወያያሉ፡፡
የፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ጋር የሚመክሩት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ የባህር ኃይል የጦር ሰፈር ሲሆን፤ የዘለንስኪ ጉብኝት እንግሊዝ ለዩክሬን ተጨማሪ እርዳታ እንደምትሰጥ ከገለጸች በኋላ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር በርንሃም እንዳሉት፤ ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን ያልተቋረጠ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም ጸረ ድሮን ቴክኖሎጂ ጭምር ለዩክሬን እንደምትሰጥ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ የኤሌክትሮኒክ የጦር መሳሪያ ድሮኖችን በራዳር እንዳይታዩ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚጓዙት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ድንበር ዘለል ጥቃቶች ተጠናክረው በቀጠሉበት ወቅት መሆኑን ኢንዲያን ቱደይ ዘግቧል።
ዘለንስኪ በቆይታቸው በዩናይትድ ኪንግደም ድጋፍ እየሰለጠኑ ካሉ 200 ያህል ዩክሬናዊያን ወታደሮች ጋር እንደሚገናኙ ነው የተገለጸው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ አስመልክቶ በተናገሩበት ወቅት፤ ዩክሬን ዘላቂ እና ፍትሃዊ ሰላም እስክታገኝ ድረስ ወደ ድጋፍ ከማድረግ ኋላ አንልም ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪዬር ስታርመር ከስልጣን ከመልቀቃቸው ከሁለት ሳምንት በፊት ኪየቭን የጎበኙ ሲሆን በስልጣን ላይ እያሉ ለዩክሬን ያልተቋረጠ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ይህ የዘለንስኪ ጉብኝት አንዲ በርንሃም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ከመጡ ወዲህ እንግሊዝን የጎበኙ የመጀመሪው የሀገር መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

