Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጋራ ሀገር የጋራ መፍትሔ – የኢትዮጵያውያን ድምጽ እኩል የሚሰማበት ምክክር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት የተለያየ የአኗኗር ሁኔታ፣ ማንነትና ባህል ባላቸው ግለሰቦች የሚገነቡ የማህበረሰብ ውቅር ውጤት ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ እይታ ቢኖራቸው ወይም ጥያቄዎቻቸውም የተለያዩ መሆናቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡

እናም የአንዱ ችግር ለሌላው ላይታየው ይችላል፤ የሌላኛውን ጥያቄ አግባብነትና መሰረታዊነት ሁሉም በእኩል ላይገነዘበው ይችላል፡፡

እነዚህ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም በሀገር ጉዳይ የጋራ መግባባትን መፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡና ለግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡

በዚህም ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ ባለፉት ዓመታት የሁሉንም ጥያቄና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራዎች ተከናውነዋል።

እስከ ወረዳ ድረስ በመውረድ አጀንዳ ማሰብሰብ፣ የአጀንዳ ልየታ እና የተሳታፊዎች ልየታ የተከናወነ ሲሆን፥ በዚህ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች መድረስ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች የሕብረተሰብ ተወካዮችን በአዲስ አበባ በማወያየት አጀንዳ ማሰባሰ ተችሏል፡፡

ሂደቱ በሀገሪቱ በሁሉም የስራ መስኮች የሚገኙ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካል እንዲሁም በበይነመረብ አማካኝነት ያለምንም ልዩነት እንዲሳተፉና አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ኢትዮጵውያን ካሉበት ቦታ ሀሳብ መስጠት እንዲችሉ ኮሚሽኑ የዲጂታል አማራጭ አዘጋጅቷል፡፡

ከዚህም ባለፈ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከምሁራን በርካታ አጀንዳዎች ተሰብስበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ባቀረቧቸው አጀንዳዎች ላይ ለሀገር የሚበጅ መግባባት ላይ ለመድረስ በአዲስ አበባ ተሰባስበው መምከር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

በዚህ ዋናው የምክክር ምዕራፍ የተበላለጠ እድል የሚኖረው አካል አይኖርም፤ ይልቁንም ሁሉም እኩል የመወሰን እድል ይሰጠዋል፡፡

ምክክሩ የተወሰኑ ሰዎችን ፍላጎት ለማስፈፀም ሳይሆን ትክክለኛ የህዝብ ችግሮችን ለመረዳት የሚያስችል ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የመጡ በመሆናቸው አንዱ የሌላውን ቁስል፣ ህመምና ስጋት እንዲረዳ እድል ይፈጥራል፡፡

ሀገር የእነዚህ ሁሉ ውቅር በመሆኗ የእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ጥያቄ ልዩነት በሌለው መልኩ ሲስተናገድ፣ ለውይይት ሲቀርብና ሲፈታ የሀገር ባለቤትነትን ስሜት ለማጎልበትና እርስ በርስ የመግባባትና የመተማመን መንፈስ ይጠናከራል፡፡

ከዚህም በላይ የማህበረሰብን ችግር በመረዳት በተደረጉ የውይይት መድረኮች የሚደረሱ የጋራ ውሳኔዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የሚኖራቸው በመሆኑ ለዘላቂ ሰላምና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ናቸው፡፡

በቤተልሔም ግርማ

Exit mobile version