አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከዚምባብዌ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሞን ሙርዊራ (ፕ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያና ዚምባብዌ ጠንካራ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት፣ በፓን አፍሪካኒዝምና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ ምልከታ ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ተነስቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች የተለዋወጧቸው የትብብር ስምምነቶች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
በተመሳሳይ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቤኒን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሪን አሞሪ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሚኒስትሮቹ ሁለቱ ሀገራት ከአሁን በፊት የተፈራረሟቸውን ሥምምነቶች ወደ ተግባር በሚለውጡባቸው አግባቦች ዙሪያ ሐሳብ ተለዋውጠዋል፡፡
ቤኒን ከኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት ማሳየቷንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ውይይቱ ከ49ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው የተካሄደው፡፡

