አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ለጋራ ልማትና ብልጽግና ያላቸው ትብብር በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፡፡
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የአዘርባጃን ብሔራዊ ም/ቤት አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ እና የልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል።
ለአዘርባጃን ልዑካን ቡድን ስለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ ያደረጉት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችንና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና አልሚዎችን የሚደግፍ ፖሊሲ በመቅረጽ ለኢንቨስትመንት ምቹና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠሯን ተናግረዋል፡፡
በግብርና፣ በማዕድንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት የገለጹ ሲሆን፥ ስኬታማ ሀገራዊ ምርጫ ማካሄዷንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁማ ምክክር ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በተለያዩ መስኮች ለጋራ ብልጽግና ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት በአዘርባጃን ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
አዘርባጃን በትምህርት፣ በአቅም ግንባታና በግብርና ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያጸና መሆኑን ጠቅሰው፥ ሀገራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

