አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቢባን ከተፈጥሮ ጋር መስማማት ከራስ ጋር ከመዋደድ ይበልጣል ይላሉ፡፡
የሰው ልጅ በምቾትና በሕይወት እንዲኖር ከሚረዳው ተፈጥሮ ጋር መስማማት አቅቶት በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የመከራ ጅራፍ መገረፍ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት በከፋ ቅዝቃዜ፣ የኑሮ ሁኔታን በሚያናጋ ከፍተኛ ሙቀት እንዲሁም በድንገተኛ ጎርፍ እና ሰደድ እሳት አደጋዎች ይታመሳሉ፡፡
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለመቆጣጠር አንዱ መፍትሔ አረንጓዴ ዐሻራን ማኖር ነው፡፡
የመደመር መንግሥት በልማት ዕቅዱ ከያዘው አበይት ነጥቦች መካከል ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት የሚለው አንዱ ጉዳይ ነው፡፡
አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳለጥ ደግሞ ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ዋናው ጉዳይ በመሆኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው ውጤታቸው መታየት ጀምሯል።
ዘንድሮም ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
አቅምን በመሰብሰብ በመደመር ዕሳቤ እየተከናወነ ያለው ይህ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው፡፡
እንደየ አካባቢው ሥነ ምህዳር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ችግኞች፣ ለደን ሽፋን፣ ለከተማ ውበትና ለማረፊያ ጥላ የሚሆኑ የአፈር መሸርሸርን የሚያስቀሩ ችግኞችን መትከል ባህል ሆኗል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአከባቢ ጥበቃ፣ በምግብ ዋሰትና፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በግብርና ምርት ውጤታማነት እንዲሁም በብዝኃ ህይወት ላይ ትልቅ አሰተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዓለምን የምታናግርበት አዲሱ ዲፕሎማሲ አረንጓዴ አሻራ ሆኗል፡፡ ይህም ለትውልድ የሚቆይ የወዳጅነት፣ የሰላምና የጋራ ኃላፊነት ምልክት ነው፡፡
በትዕግስት ግዛቸው

