አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም በተፈጥሮ ሀብት መመናመንና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እያስተናገደቻቸው ያሉ አሉታዊ ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ይህንን ተግዳሮት ለመቋቋም የተፈጥሮ ሚዛንን መጠበቅና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሁለንተናዊ ገጽታዋን ከመቀየር ባለፈ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያሳደገ ይገኛል፡፡
በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ትልቅ ሃገራዊ ስኬት ማስመዝገብ ችሏል።
መርሐ ግብሩ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማገገም፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና የደን ሽፋንን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ይህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ደግሞ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ ከሆነው ከግብርና ዘርፍ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ንቅናቄ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
በየዓመቱ የሚተከሉት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመግታት ለም አፈር እንዲጨምር ምክንያት ሆነዋል፡፡
ይህም የመሬትን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲበለጽግ በማድረግ ለመስኖና ግብርና ሥራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
መርሐ ግብሩ ከጥላና ከደን ዛፎች ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን እንደ አቮካዶ፣ ማንጎና ፓፓያ ያሉትን በማካተት የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ አስተዋዕጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢን ተፈጥሯዊ ገጽታ ለመጠበቅ እንዲሁም ንጹህ አየርና ውሃ እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ የተዘረጋ ጠንካራ መሠረት ነው።
ይህ ንቅናቄ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባትና ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን ለማድረግ የሚደረገውን ሃገራዊ ጉዞ በከፍተኛ ደረጃ እያገዘ ይገኛል።
በሶስና አለማየሁ

