አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በአደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት የተጠረጠረውን አድነው ባሻው በቁጥጥር ሥር ውሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ አድርጓል።
በማላዊ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው በበርካታ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ላይ ከባድ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽም መቆየቱ ተገልጿል።
አድነው ባሻው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም ከሀድያ እና ከንባታ ዞኖች በርካታ ወጣቶችን ሕይወት እንደሚያሻሽል በመሐላና በአጉል ተስፋ በማታለል በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያዘዋውር መቆየቱን በሰውና በሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን ፖሊስ አመልክቷል።
ተጠርጣሪው ከእያንዳንዱ ተጓዥ ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር የሚጠይቅ ሲሆን፤ በቅድመ ክፍያ ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ ሲቀበል መቆየቱንም የምርመራ መዝገቡ ጠቁሟል።
ተጓዦችን በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በማሻገር በጋንቦ ጫካ ውስጥ በድብቅ በማስቀመጥ በየ 24 ሰዓት ትንሽ ሩዝ ከቁራጭ ዳቦ ጋር ብቻ በመስጠት፣ በከፍተኛ ረሃብና የውሃ ጥም እንዲሰቃዩ ከማድረጉም በላይ በሞተርና በእግር ሴሎ በረሃን ጭምር እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል ሲል ፖሊስ ገልጿል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጎዦችን በሕገ-ወጥ መንገድ ናይሮቢ ከተማ ካደረሳቸው በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ በማጎር፣ ተጨማሪ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው እንዲያስልኩ በማስገደድ ከፍተኛ ግፍ መፈጸሙን ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማረጃ ደርሼበታለሁ ብሏል።
ከቤተሰብ ገንዘብ ማስላክ ያልቻሉትን ተጓዦችን በመደብደብና “እዚሁ ትሞታላችሁ” እያለ በማስፈራራት እንዲሁም በኤሌክትሪክ ንዝረት በማሰቃየት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በመፈጸም ተጨማሪ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ግብረ አበሮቹ በኩል በባንክ እንዲከፈለው አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ ከናይሮቢ በዕቃ መጫኛ ኮንቴነሮች፣ በተሳቢና ከኋላ ክፍት በሆኑና በሸራ በተሸፈኑ መኪኖች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተጓዦችን በመጫን ታንዛኒያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ጥሎ በመጥፋት ለአሰቃቂ አደጋ ዳርጓቸዋል ሲል ፖሊስ ገልጿል።
አብዛኞቹ ወጣቶች ደቡብ አፍሪካ ሳይደርሱ በተለያዩ ሀገራት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር በመግባታቸው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡና እስራቱን ሲጨርሱም እስከ 170 ሺህ ብር ከፍለው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል በበርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽምና የኢኮኖሚ ጉዳት ሲያደርስ የቆየውን አድነው ባሻው ውዳሞን የማላዊ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ አሳልፎ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጋር በመተባበር በተመሳሳይ ወንጀል ላይ የተሰማሩትን አድኖ ለሕግ የማቅረብ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ ኅብረተሰቡ በEFPApp፣ በ991 እና በSPS መረጃ በመስጠት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

