Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዛሬው ምክክር የነቃ ተሳትፎ የነገዋን ጠንካራ ሀገር በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያግዛል

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን መዋቅራዊና ታሪካዊ ቅራኔዎች በዘላቂነት ለመፍታትና የጋራ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች።
የዚህ ታሪካዊ መድረክ ስኬት መሠረቱ ደግሞ የዜጎችና የተመካካሪዎች ንቁ ተሳትፎ ነው።
ይህ ተሳትፎ ዛሬ ላይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ከመቅረፍ ባለፈ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራና አስተማማኝ ሀገር ለማስረከብ ትልቅ ተስፋን እየፈጠረ ይገኛል።
ይህንን ከግምት ያስገቡት ተመካካሪዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካና የማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ዜጎች ቅሬታዎቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በኃይል ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት ማቅረብ መጀመራቸው ውይይትን ብቸኛ የችግር መፍቻ መንገድ ያደርገዋል።
በምክክሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ መድረክ ተቀምጠው መደማመጣቸው በትውልዶች መካከል የሰላም ባህል እንዲሰርጽ ያደርጋል።
ይህም የኢትዮጵያን ቀጣይ ጥንካሬ ሁሉንም በሚያስማማ የጋራ ሀገራዊ ትርክት ላይ ለመገንባት ያስችላል።
ከተለያዩ የኑሮ፣ የባህልና የፖለቲካ አመለካከቶች የመጡ ተመካካሪዎች በነፃነት መሳተፋቸውም የተናጠል ጥቅምን ወደ ጋራ ሀገራዊ ጥቅም ይለውጠዋል።
የሕዝብ ድምፅ በንቃት የተደመጠበት ምክክር የሚያመጣው ውጤት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል።
ይህም ለቀጣዩ ትውልድ የቅሬታ ምንጭ የማይሆን የሕግና የፖሊሲ መሠረትን ይጥላል።
ምክክሩ ጠንካራ ማኅበራዊ ውል እና ተቋማትን ለመገንባት ያግዛል፡፡
እንደሚታወቀው ጠንካራ ሀገር የምትገነባው በግለሰቦች ጥረት ብቻ ሳይሆን በማይናወጡ ሀገራዊ ተቋማት ነው።
ሕዝቡ ራሱ ተሳትፎበት የሚፈጥራቸው ተቋማት ገለልተኛ፣ ጠንካራ እና ለሕግ የበላይነት የሚገዙ እንዲሆኑም መሠረት ይጥላል።
ንቁ ምክክሩ ዜጎች ከሀገራቸውና ከመንግሥት ጋር ያላቸውን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚደነግግ አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ ለመቅረጽ ያስችላል።
ታሪካዊ ስህተቶች ሳይታረሙና ቁርሾዎች ሽረው ሳይድኑ ለቀጣይ ትውልድ ከተላለፉ፣ ሀገርን የማዳከም አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ሀገራዊ ምክክሩም ይህንን አዙሪት ይሰብራል።
የዛሬው ትውልድ የትላንትና የዛሬ ችግሮችን በውይይት ሲዘጋ፣ ቀጣዩ ትውልድ የፖለቲካ እሰጥ አገባ ውስጥ ሳይገባ ትኩረቱን በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ብቻ እንዲያደርግ ዕድል ይሰጠዋል።
የወደፊቱ ትውልድ አባቶቹና እናቶቹ ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ እንደፈቱ ሲያውቅ፣ በሀገሩ የመኩራትና የአንድነት ስሜቱ ይጎለብታል።
የሀገራዊ ምክክሩ ተመካካሪዎች የሚያሳዩት ንቁ ተሳትፎ የዛሬውን የቤት ሥራ ለመሥራት ብቻ አይደለም፤ የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ነው።
ዛሬ በምክክር መድረኮች ላይ የሚዘሩት የሃሳብ፣ የመቻቻልና የአንድነት ፍሬዎች ነገ ለቀጣዩ ትውልድ የምትበለጽግ፣ ሰላሟ የተጠበቀና ጠንካራ ሀገርን ለማስረከብ አስተማማኝ ብሩህ ተስፋዎች ናቸው።
Exit mobile version