አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ55 ሚሊየን በላይ ዜጎች የህክምና አገልግሎት አግኝተዋል አለ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት።
አገልግሎቱ የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃፀም ግምገማ በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ በ1ሺህ 279 ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ10 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሀገር አቀፍ የጤና መድህን አባል መሆናቸውንና ከ55 ሚሊየን በላይ ሰዎች የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ለህክምና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ መፈፀሙን ጠቁመዋል።
ክፍያ ከሚከፍሉ አባላት በተጨማሪ መክፈል የማይችሉ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ነው ያመለከቱት።
በጳውሎስ አየለ

